ቀጥታ፡

በጠቅላላ ምርጫው ድምፅ ለመስጠት ዕለቱን በጉጉት እየተጠባበቅን ነው - የደገሀቡር ከተማ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2018(ኢዜአ)፦ ግንቦት 24/2018 ዓም በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት ዕለቱን በጉጉት እየተጠባበቁ መሆኑን የደገሀቡር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት 54 ሚሊየን 57 ሺህ 861 መራጮች መመዝገባቸውን አስታውቋል።

በሶማሌ ክልል የደገሀቡር ከተማ ነዋሪዎችም፤ በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን ካርድ በመውሰድ ዕለቱን እየተጠባበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ የደገሀቡር ከተማ ነዋሪዎች መካከል ሳሚ ረዲ፤ ለመራጭነት የሚያበቃውን የምርጫ ካርድ በመውሰድ በዕለቱ ድምፅ ለመስጠት ቀኗን እየተጠባበቀ መሆኑን አስታውቋል።

ሰኞ የሚካሄደውን ምርጫ በጉጉት እየተጠባበቀ መሆኑን ገልጾ፤ ለዚህም በማለዳ በሚመርጠበት ጣቢያ እንደሚገኝ ተናግሯል።

ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ ሰኢድ መሀመድ በበኩላቸው፤ ድምፅ በሚሰጥበት ዕለት ሰኞ በማለዳ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያውያንም በምርጫው ዕለት በማለዳ በመነሳት የወሰዱትን የምርጫ ካርድ በመጠቀም በዕለቱ በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት መምረጥ እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

ለመራጭነት የሚያበቃኝን ካርድ አስቀድሜ መያዝ ችያለሁ ያሉት ደግሞ ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ ሱልጣን ሻከር አብዲ ናቸው።

የምርጫውን ቀን በጉጉት በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን በመጠቆም፤ በዕለቱ በማለዳ በመነሳት ይበጀኛል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።

በሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ይበጀኛል የምለውን ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ነኢማ ከይሩ ናት።

ዕለቱንም በጉጉት እየተጠባበቀች መሆኑን ተናግራለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም