በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የምርጫ ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እየተሰራጨ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የምርጫ ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እየተሰራጨ ነው
ወላይታ ሶዶ፤ ግንቦት 22/2018 (ኢዜአ):-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለሚገኙ ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ቁሳቁስ እየተሰራጨ መሆኑን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
ከነገ በስቲያ ለሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጻቸውን ለመስጠት 54 ሚሊዮን 57 ሺህ 861 ዜጎች ተመዝግበው የምርጫውን ቀን እየተጠባበቁ ነው።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስፈልጉ የምርጫ ቁሶችም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በየምርጫ ጣቢያዎች የማድረስ ሥራ እየተከናወነ ነው።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለሚገኙ ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎችም ቁሳቁሱን የማሰራጨት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም አንጁሎ ተናግረዋል።
ኃላፊው እንደገለጹት በመጪው ሰኞ በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ አስፈላጊው የዝግጅት ሥራዎች በተደራጀ መልኩ ሲከናወኑ ቆይቶ፣ በአሁኑ ወቅት በምርጫ ቦርድ መርሀግብር መሰረት የምርጫ ቁሳቁስ ወደምርጫ ጣቢያዎች እየተሰራጨ ይገኛል።
ቁሳቁሱ እየተሰራጨ ያለው በክልሉ ባሉ 56 የምርጫ ክልሎች ስር ወደሚገኙ 3 ሺህ 941 የምርጫ ጣቢያዎች መሆኑንም አቶ አብርሃም አስታውቀዋል።
በወላይታ ዞን የሶዶ ዙሪያ-2 ምርጫ ክልል አስተባባሪ አቶ ምህረቱ ጋዴቦ በበኩላቸው እንዳሉት በምርጫ ክልሉ ሥር ለተደራጁ 108 የምርጫ ጣቢያዎች የቁሳቁስ የማሰራጨት ሥራ እየተከናወነ ነው።
የቁሳቁስ ስርጭቱ ደህንነቱ በተጠበቀና አስተማማኝ በሆነ መንገድ እየተከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ እንደሚያሳየው በመጪው ሰኞ የሚካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚፎካከሩበት መሆኑ ታውቋል።