ቀጥታ፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በወልቂጤ የምርጫ ክልል የቁሳቁስ ስርጭት እየተከናወነ ነው

ወልቂጤ ፤ ግንቦት 22/2018 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በወልቂጤ ምርጫ ክልል ወደ ተለያዩ ምርጫ ጣቢያዎች የቁሳቁስ ስርጭት እየተከናወነ መሆኑን የምርጫ ክልሉ አስተባባሪ አቶ ሲሳይ ጀማል ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል አስፈላጊው ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን በገለጸበት ወቅት የምርጫ ቁሳቁስን የማሰራጨት ተግባር በጊዜ ሰሌዳው መሰረት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሷል።

በዚህም በተለያዩ አካባቢዎች የምርጫ ቁሳቁስ ስርጭቱ ያለምንም እንከን እየተከናወነ መሆኑንም ቦርዱ ገልጿል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ የምርጫ ክልሎችም የፊታችን ሰኞ ግንቦት 24/2018 ዓ.ም ለሚካሄደው ምርጫ ወደ ምርጫ ጣቢያዎቹ የምርጫ ቁሳቁስ የማሰራጨት ተግባሩ በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል። 

በክልሉ ወልቂጤ ምርጫ ክልል አስተባባሪ አቶ ሲሳይ ጀማል እንደገለፁት፤ በምርጫ ክልሉ ለሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች የድምጽ መስጫ ቁሳቁስ በመሰራጨት ላይ ነው።

ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ለድምጽ መስጫው እለት ዝግጁ መደረጋቸውን ጠቅሰው የቁሳቁስ ስርጭቱ ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ለድምፅ መስጫ ሂደቱ ዝግጁ የሆኑ ቁሳቁሶችም የምርጫ ሳጥኖችን፣ የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን እና ሌሎችን የሚያካትቱ መሆናቸውን አስተባባሪው አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም