በካርዳችን በምርጫው እለት ድምፅ በመስጠት ቀጣይ መሪዎቻችንን ለመምረጥ ተዘጋጅተናል - ኢዜአ አማርኛ
በካርዳችን በምርጫው እለት ድምፅ በመስጠት ቀጣይ መሪዎቻችንን ለመምረጥ ተዘጋጅተናል
ምዕራብ ወለጋ፤ ግንቦት 22/2018 (ኢዜአ)፦ በወሰድነው ካርድ በምርጫው እለት ድምፅ በመስጠት ቀጣይ መሪዎቻችንን ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ሲሉ በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ።
የፊታችን ሰኞ የሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚፎካከሩበትና 54 ሚሊየን 57 ሺህ 861 መራጮች የተመዘገቡበት ታሪካዊ የምርጫ ሂደት ነው።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የተሟላ ዝግጅት በማድረግ የምርጫ ሂደቱ እየተከናወነ ሲሆን ግንቦት 24 እለተ ሰኞ ከማለዳው ጀምሮ ድምፅ የሚሰጥ ይሆናል።
በዚሁ መሰረትም በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ወለጋ ዞን የሆማ ወረዳ እና ጊምቢ ወረዳዎች ነዋሪዎች የሚፈልጉትን ፓርቲ ለመምረጥ የድምፅ መስጫውን እለት እየተጠባበቁ መሆኑን ገልጸዋል።
በዞኑ የሆማ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ኢናኑ መልካሙ እና ወይዘሮ ወርቅነሽ አቶምሳ እንዲሁም የጊምቢ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ታደለች ታረቀኝ፤ በምርጫ ሂደት በተለይም የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ የወሰድነውን ካርድ በምርጫው እለት ድምፅ በመስጠት ቀጣይ መሪዎቻችንን ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ሲሉ ተናግረዋል።
ለምርጫው የመራጮች ትምህርት ለሚሰጡ 169 ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንዲሁም ምርጫውን ለሚታዘቡ 55 የሀገር ውስጥ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ፈቃድ የተሰጣቸው መሆኑ ይታወቃል።