ኢጋድ በሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ 26 የምርጫ ታዛቢዎችን አሰማርቷል - ኢዜአ አማርኛ
ኢጋድ በሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ 26 የምርጫ ታዛቢዎችን አሰማርቷል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2018 (ኢዜአ)፦ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) በሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ በተለያዩ አካባቢዎች 26 የምርጫ ታዛቢዎች ማሰማራቱን አስታወቀ።
በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የሰላምና ደህንነት ዘርፍ ዳይሬክተር ኮማንደር አበበ ሙሉነህ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ የሚታዘቡ አካላት ተሰማርተዋል።
ከኢጋድ ሴክሬታሪያትና አባል ሀገራት የተውጣቱ 26 ታዛቢ ሙያተኞች የምርጫ ሂደቱን እንዲታዘቡ ማሰማራቱን አስታውቀዋል።
የምርጫ ታዛቢዎችም በአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ከአባል ሀገራት የምርጫ ቦርድና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀቶች ጋር በቀጥታ የሚሰሩ ሙያተኞች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም በ7ኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ የተሰማሩ ታዛቢዎችም የምርጫ ቦርድ ሙያተኞችና ኃላፊዎች ጭምር በተመረጡ አካባቢዎች የታዛቢነት ስምሪት መሰጠቱን ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት ብቻ የዑጋንዳንና ጂቡቲን የአባል ሀገራት የምርጫ ሂደት መታዘቡን ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅትም 7ኛውን የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ እየታዘበ እንደሚገኝ አስንተዋል።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ለጠቅላላ ምርጫው በሚያደርገው ቅድመ ዝግጅት የታዛቢነት መስፈርት በማሟላት ምዝገባ አካሂደውና ቃለ ማሃላ በመፈፀም ወደሥራ መግባቱንም አብራርተዋል።
ምርጫ ቦርድ ለምርጫ ታዛቢነት ለተዘጋጁ አካላት የኢትዮጵያን የምርጫ ሕግና ሌሎች የአሰራር ደንቦችን የተመለከተ ስልጠና በመስጠት ፈቃድ መስጠቱን አንስተዋል።