ቀጥታ፡

በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ምርጫ ክልል የድምጽ መስጫ ቁሳቁስ እየተሰራጨ ነው

ገንዳ ውሃ እና ደብረ ብርሃን ፤ ግንቦት 22/2018 (ኢዜአ)፦ በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ምርጫ ክልል ስር ወደሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች የድምጽ መስጫ ቁሳቁስ ስርጭት እየተከናወነ መሆኑ ተገለፀ።

በተመሳሳይ በደብረ ብርሃን ምርጫ ክልልም የምርጫ ቁሳቁስ እየተሰራጨ መሆኑ ተመላክቷል።

በዞኑ የመተማ ምርጫ ክልል አስተባባሪ አቶ መሰረት ዋስይሁን እንደገለጹት፣ ከነገ በስቲያ ለሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምጽ መስጫ ቁሳቁስ ከትናንት ጀምሮ ወደምርጫ ጣቢያዎች የማሰራጨት ሥራ እየተከናወነ ነው።  

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የምርጫ ቁሶቹ እየተሰራጩ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዛሬው እለትም ወደ ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የማድረስ ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል። 

የምርጫ ቁሳቁስ ደህንነታቸውና ሚስጥራዊነታቸውን በጠበቀ አግባብ ወደ ምርጫ ጣቢያዎቹ ከመላክ ባለፈ በምርጫ ጣቢያዎች መድረሳቸውን እየተረጋገጠ መሆኑንም ተናግረዋል።  

እንደ አስተባባሪው ገለጻ በምርጫ ክልሉ 92 የምርጫ ጣቢያዎች እና 2 ንዑስ ጣቢያዎች ይገኛሉ።

በተመሳሳይ በደብረ ብርሃን ምርጫ ክልል ስር ወደሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎችም ለድምጽ መስጫ አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁስ የማድረስ ሥራ እየተከናወነ ነው። 

ሰኞ ግንቦት 24 ለሚካሄደው 7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ የምርጫ ጣቢያዎችን ለድምፅ አሰጣጥ ሂደት ምቹና ዝግጁ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑም ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ እንደሚያሳየው ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ 54 ሚሊዮን 57 ሺህ 861 መራጮች መመዝገባቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም