ቀጥታ፡

በድምጻችን የነገ መሪዎቻችንን ለመምረጥ የድምጽ መስጫ ቀኑን እየጠበቅን ነው - የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች

ጂንካ፤ ግንቦት 22/2018(ኢዜአ)፦ በካርዳቸው ድምጻቸውን በመስጠት የነገ መሪዎቻቸውን ለመምረጥ የምርጫውን ቀን እየተጠባበቁ መሆናቸውን የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፊታችን ሰኞ ግንቦት 24/2018 ዓም ይካሄዳል።

ለጠቅላላ ምርጫው የወሰዱትን ካርድ ተጠቅመው ድምጻቸውን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የጂንካ ከተማ አስተያየት ሰጪዎች ገልጸዋል፡፡

ከአስተያየት ሰጪዎቹ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ መኩሪያ ጌታቸው እንዳሉት፣ በካርዳቸው የነገ መሪዎቻቸውን ለመወሰን የምርጫውን እለት በጉጉት እየተጠባበቁ ናቸው።

ከእሳቸው በተጨማሪ ባለቤታቸውና ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ የምትሳተፈው የበኩር ልጃቸው በጠቅላላ መርጫው ድምጻቸውን ለመስጠት የምርጫውን ቀን እየተጠባበቁ መሆኑን ተናግረዋል።

ወይዘሮ ዝናሽ ካሳ እና አቶ ገዛኸኝ አልሻይ በበኩላቸው በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ድምጻቸው ዋጋ እንዳለው በመገንዘብ በእለቱ ማልደው በመነሳት ድምጻቸውን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላላ ምርጫው መሪዎቻቸውን በድምጻቸው ለመወሰን እንደሚያስችላቸው የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ በምርጫው ታሪካዊ አሻራቸውን ለማሳረፍ ዕለቱን በጉጉት እየጠበቁ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም