በምርጫው ዕለት በነቂስ ወጥተን ይበጀናል ለምንለው ፓርቲ ድምጽ ለመስጠት ተዘጋጅተናል -የጅማ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በምርጫው ዕለት በነቂስ ወጥተን ይበጀናል ለምንለው ፓርቲ ድምጽ ለመስጠት ተዘጋጅተናል -የጅማ ከተማ ነዋሪዎች
ጅማ፤ ግንቦት 22/2018 (ኢዜአ)፦ በምርጫው ዕለት በነቂስ ወጥተን ይበጀናል ለምንለው ፓርቲ ድምጽ ለመስጠት ተዘጋጅተናል ሲሉ ኢዜአ የነጋገራቸው የጅማ ከተማ ነዋሪዎች ተናግሩ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፊታችን ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።
ኢትዮጵያውያን በምርጫው ለመሳተፍ እለቱን በጉጉት እየጠበቁ መሆናቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
ይህንኑ አስመልክቶ ሐሳባቸውን ለኢዜአ የሰጡ የጅማ ከተማ ነዋሪዎች፤ በዕለቱ በነቂስ ወጥተው ይበጀናል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የከተማዋ ነዋሪ አቶ ነኢም ነጋሽ በሰጡት አስተያየት፣ "ለእኔ፣ ለልጆቼና ለሀገሬ ይበጃል ያልኩትን ፓርቲ ለመምረጥ ዝግጁ ነኝ" ብለዋል።
ድምፃቸው ትልቅ ዋጋ እንዳለውና የነገውን ዕጣ ፈንታ እንደሚወስን በመገንዘብ በዕለቱ ቀድመው ድምፅ ለመስጠት መወሰናቸውን ተናግረዋል።
ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ታደለች ተሰማ በበኩላቸው፣ የድምፅ መስጫውን ዕለት በጉጉት እየተጠባበቁ መሆኑን ገልጸዋል።
የአንድ ሰው ድምፅ ዋጋ እንዳለው በመረዳት ሁሉም ዜጋ ግንቦት 24 ቀን ወጥቶ ሀገርን ያስቀጥላል፣ ይጠቅማል ያለውን አካል እንዲመርጥም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ለሀገራችን ዕድገትና ሰላም ይበጃል ያልነውን ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ያሉት ደግሞ ወጣቶቹ ደቻሳ ጋዲሳ እና ትርሲት ተሾመ ናቸው።
ሀገር የምትገነባው በዜጎቿ ድምፅ እና ጥረት ነው። ድምፃችን ትልቅ ዋጋ አለው፤ ለዲሞክራሲ ስርዓት እና ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ወሳኝ በሆነው በዚህ ምርጫ ላይ በመሳተፍ የዜግነት ግዴታችንን እንወጣለን ብለዋል።
በመጨረሻም ሁሉም ድምፅ የመስጠት መብት ያለው ዜጋ በዕለቱ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በመሄድ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።