የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የመልስ ጨዋታውን ከብሩንዲ ጋር ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የመልስ ጨዋታውን ከብሩንዲ ጋር ያደርጋል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2018 (ኢዜአ)፦ በ2026 ከ17 ዓመት በታች ሴቶች የዓለም ዋንጫ የሁለተኛ ዙር ማጣሪያ ኢትዮጵያ ከብሩንዲ ጋር ዛሬ የመልስ ጨዋታዋን ታከናውናለች።
የሀገራቱ ጨዋታ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በኢንትዋሪ ስታዲየም ይካሄዳል።
ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ግንቦት 16 ቀን 2018 ዓ.ም በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ 2 ለ 1 አሸንፋለች።
ሊዲያ እያሱ ግቦቹን ለኢትዮጵያ አስቆጥራለች። አኒታ ንዲኩማና የብሩንዲ ብቸኛ ግብ ከመረብ ላይ አሳርፋለች።
በራውዳ አሊ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የመልስ ጨዋታውን ለማድረግ ወደ ቡጁምቡራ ግንቦት 19 ቀን 2018 ዓ.ም አምርቷል።
ብሔራዊ ቡድኑ ለቀናት ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቶ የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት ጨዋታው በሚደረግበት በኢንትዋሪ ስታዲየም አድርጓል።
ሁሉም ተጫዋቾች በሙሉ ጤንነት እና የጨዋታ ዝግጁነት ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
በፓትሪክ ሳንጋዋ የሚመራው የብሩንዲ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከኢትዮጵያ ጋር ለሚያደርገው የመልስ ጨዋታ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል።
ኢትዮጵያ በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈች በመጨረሻው ዙር ማጣሪያ ከዛምቢያ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አሸናፊ ጋር ትጫወታለች።
10ኛው የፊፋ የሴቶች ከ17 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ በጥቅምት ወር 2019 ዓ.ም በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይካሄዳል።
በውድድሩ ላይ 24 ሀገራት ይሳተፋሉ። በዓለም ዋንጫው አፍሪካ ሞሮኮን ጨምሮ በአምስት ሀገራት ትወከላለች። ቀሪ አራት ሀገራት በማጣሪያ ጨዋታዎች ይለያሉ።