የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከአዳማ ከተማ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከአዳማ ከተማ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ34ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ከቀኑ ሰባት ሰዓት ሲዳማ ቡና ከአዳማ ከተማ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሲዳማ ቡና በ58 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው። አዳማ ከተማ በ39 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዟል።
በ33ኛ ሳምንት አርባምንጭ ከተማን 3 ለ 0 በመርታት ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ሲዳማ ቡና ሶስት ነጥብ ማግኘት መሪነቱን ያጠናክርለታል።
ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋተታዎች አንዱን በማሸነፍ የመውረድ ስጋት ውስጥ የገባው አዳማ ከተማ በሊጉ ለመቆየት በሚያደርገው ጉዞ ከዛሬው ጨዋታ ሶስት ነጥብ ማግኘት ግድ ይለዋል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ መድን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ40 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ተጋጣሚው ኢትዮጵያ መድን በ42 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዟል።
በ33ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከአዳማ ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል።
የወቅቱ የሊጉ የዋንጫ ባለቤት ኢትዮጵያ መድን ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።
ሁለቱ ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ እና ወራጅ ከመሆን ስጋት ለመላቀቅ የሚያደርጉት ፍልሚያ ይጠበቃል።
ከቀኑ 10 ሰዓት መቀሌ 70 እንደርታ ከባህር ዳር ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።
መቀሌ 70 እንደርታ በ34 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ባህር ዳር ከተማ በ45 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በ33ኛ ሳምንት መርሐ ግብር መቀሌ 70 እንደርታ ሸገር ከተማን 1 ለ 0 አሸንፏል። ባህር ዳር ከተማ ደግሞ ከመቻል ጋር አንድ አቻ ተለያይቷል።
መቀሌ 70 እንደርታ ሶስት ነጥብ ማግኘት ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት በሚያደርገው ትግል ወሳኝ ነው።
ተጋጣሚው ባህር ዳር ከተማ ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ ይጫወታል።
ባህር ዳር ከተማ በሊጉ በበርካታ ጨዋታዎች (18 ጊዜ) አቻ የወጣ ቡድን ነው።
በተያያዘም ትናንት በዝናብ ምክንያት የተቋረጠው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ ዛሬ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ከ30 በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ከቆመበት ደቂቃ አንስቶ ይቀጥላል።
ጨዋታው በአዲስ አበባ ስታዲየም እየተካሄደ በ30ኛው ደቂቃ በከባድ ዝናብ ምክንያት መቋረጡ ይታወቃል።
እስከተቋረጠበት ሰዓት በጨዋታው ላይ ምንም ግብ አልተቆጠረም።