ቀጥታ፡

ፒኤስጂ እና አርሰናል ለሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ፤ የአምናው አሸናፊ ከታሪክ ፈላጊው ጋር

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2018 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፒኤስጂ እና አርሰናል ዋንጫውን ለማንሳት የሚያደርጉት ፍልሚያ የዓለም እግር ኳስ አፍቃሪያንን ቀልብ ስቧል።

ጨዋታው በሃንጋሪ ቡዳፔስት፣ 67 ሺህ ተመልካቾችን በሚይዘው ፑሽካሽ አሬና ስታዲየም ምሽት አንድ ሰዓት ላይ ይጀምራል።

በግማሽ ፍጻሜው ፒኤስጂ ባየር ሙኒክን፣ አርሰናል ደግሞ አትሌቲኮ ማድሪድን በድምር ውጤት በመርታት ለታላቁ የፍጻሜ ጨዋታ ደርሰዋል።

ፒኤስጂ በዘንድሮው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ባደረጋቸው 16 ጨዋታዎች ዘጠኙን ሲያሽንፍ በሁለቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ አምስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።

በጨዋታዎቹ ላይ 44 ግቦችን ሲያስቆጥር 22 ጎሎች ተቆጥረውበታል።

የወቅቱ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ባለቤት ፒኤስጂ ያስቆጠራቸው ጎሎች ብዛት የማጥቃት አቅሙ ጠንካራ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው።

ተጋጣሚው አርሰናል በዘንድሮው ሻምፒዮንስ ሊግ ምንም ጨዋታ ሳይሸንፍ ለፍጻሜ ደርሷል። ካደረጋቸው 14 ጨዋታዎች መካከል በ11ዱ ድል ሲቀናው በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል።

በጨዋታዎቹ ላይ 29 ግቦችን ሲያስቆጥር ስድስት ጎሎችን ብቻ አስተናግዷል።

መድፈኞቹ ከ14ቱ ጨዋታዎች መካከል በዘጠኙ ግብ አለማስተናገዳቸው የተከላካይ መስመር እና አጠቃላይ ጥንካሬ አጉልቶ የሚያሳይ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሲገናኙ የአሁኑ ለስድስተኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች ፒኤስጂ ሁለቱን ሲያሸንፍ አርሰናል አንድ ጊዜ ድል ቀንቶታል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።

በአምስቱ ጨዋታዎች ሁለቱም በተመሳሳይ ስድስት ግቦችን ከመረብ ጋር አገናኝተዋል።

ሁለቱ ቡድኖች በውድድሩ የተገናኙት እ.አ.አ በ2024/25 የውድድር ዓመት በግማሽ ፍጻሜ ላይ ነበር።

በወቅቱ ፒኤስጂ በድምር ውጤት 3 ለ 1 (1 ለ 0 እና 2 -1) በማሸነፍ ለፍጻሜ ያለፈ ሲሆን በፍጻሜው ኢንተር ሚላንን 5 ለ 0 በመርታት የአውሮፓውን ክብር ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀዳጅቷል።

ከግማሽ ፍጻሜው በፊት በሊግ ምዕራፍ (League Phase) ተገናኝተው አርሰናል 2 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

ፒኤስጂ ለአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ሲደርስ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው። የፓሪሱ ክለብ የአውሮፓ ክብሩን ለማስጠበቅ ይጫወታል።

አርሰናል ከ20 ዓመታት በኋላ ለፍጻሜው ያለፈ ሲሆን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫውን ለማንሳት ይፋለማል።

መድፈኞቹ ከዚህ ቀደም እ.አ.አ በ2006 ለፍጻሜ ደርሰው በባርሴሎና 2 ለ 1 ተሸንፈው ዋንጫውን ማጣታቸው የሚታወስ ነው።

የፒኤስጂው የክንፍ መስመር ተጫዋች ክቪቻ ክቫራትስኬሊያ በዘንድሮው ውድድር 10 ግቦችን ማስቆጠር እና ስድስት ጎሎችን አመቻችቶ በማቀበል የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች መሆኑን አስመስክሯል።

ክቫራትስኬሊያ የዓለማችን ምርጡ የክንፍ መስመር ተጫዋች በመባል እየተሞከሸ ይገኛል።

የወቅቱ የባለንዶር አሸናፊ ኡስማን ዴምቤሌ ሰባት ግቦችን በማስቆጠር እና ሶስት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል ሌላኛው የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች መሆኑን አሳይቷል።

በዘንድሮው ሻምፒዮንስ ሊግ ለአርሰናል በርካታ ግቦችን ያስቆጠረው ጋብርኤል ማርቲኔሊ ነው። ስድስት ግቦችን ከማስቆጠሩም ባለፈ ለሶስት ግቦች መቆጠር ምክንያት ሆኗል።

ስዊድናዊው አጥቂ ቪክቶር ዮኮሬሽ አምስት ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ በሁለት ግቦች መቆጠር ላይ ደግሞ አስተዋጽኦ አድርጓል።

የተጠቀሱት ተጫዋቾች በጨዋታው ላይ ልዩነት ሊፈጥሩ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ፍልሚያው በማጥቃት አቅሙ በሚታወቀው ፒኤስጂ እና በመከላከል ጥንካሬው በሚደነቀው አርሰናል መካከል የሚደረግ በመሆኑ 'የማጥቃት እና የመከላከል ፍጥጫ' የሚል ስያሜ አግኝቷል።

ፒኤስጂ ክብሩን ለማስጠበቅ፣ አርሰናል ለመጀመሪያ ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ለመሆን የሚያደርጉት ጨዋታ የዓለምን ትኩረት ስቧል።

የ42 ዓመቱ ጀርመናዊ ዳንኤል ሲበርት ተጠባቂውን የፍጻሜ ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም