ቀጥታ፡

ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ 54 ሚሊየን 57 ሺህ 861 መራጮች ተመዝግበዋል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2018(ኢዜአ)፦ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ 54 ሚሊየን 57 ሺህ 861 መራጮች መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሃይሉ፤ በመጪው ሰኞ የሚካሄደውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ምርጫውን ለማካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

ቦርዱ ለመጀመሪያ ጊዜ ባዘጋጀው የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር መድረክ ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውንና አማራጭ ሃሳባቸውን ለመራጩ ህዝብ እንዲያቀርቡ መደረጉን አብራርተዋል።

በመመሪያው መሰረትም ለፖለቲካ ፓርቲዎች የአየር ሰዓት ድልድል ተደርጎ ፓርቲዎች ሃሳቦቻቸውን ለህዝብ ተደራሽ ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል።

የመራጮች ትምህርት ለሚሰጡ 169 ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቦርዱ ፈቃድ መስጠቱን ጠቁመው ምርጫውን ለሚታዘቡ 55 የሀገር ውስጥ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንዲታዘቡ ፈቃድ መስጠቱን አስረድተዋል።

ከአፍሪካ ህብረት 59 አባላት ያሉት ታዛቢዎች ቡድን መምጣቱን ገልጸው፤ ከኢጋድ ደግሞ 26 አባላት ያሉት ቡድን እንደሚታዘቡም አክለዋል።

ቦርዱ በጥቅሉ ለ68 መገናኛ ብዙሃን ምርጫውን እንዲዘግቡ ፈቃድ መስጠቱን ጠቁመው ከዚሁ ወስጥ 56 የሀገር ውስጥ ሲሆኑ 12 ደግሞ የውጭ መገናኛ ብዙሃን መሆናቸውን ገልፀዋል።

የቁሳቁስ ስርጭቱ ቀድሞ በተያዘው መርሐ ግብር መሠረት በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑንና የቁሳቁስ ስርጭቱ በተያዘለት ጊዜ ሙሉ በሙሉ ተደራሽ ሆኖ የምርጫ ጣቢያዎች ለምርጫው ሙሉ ዝግጅታቸውን እንደሚያጠናቅቁ ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።

በምርጫው ድምጽ ለመስጠት 54 ሚሊየን 57 ሺህ 861 መራጮች መመዝገባቸውን ጠቁመዋል።

በመመሪያው መሰረትም የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ መቋቋሙን ሰብሳቢዋ ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም