ቀጥታ፡

ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2018(ኢዜአ)፦ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

የምርጫ ቁሳቁሶችን የማሰራጨት ሥራም በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እየተከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሃይሉ፤ በመጪው ሰኞ የሚካሄደውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ምርጫውን ለማካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው ብለዋል።

ቦርዱ ለመጀመሪያ ጊዜ ባዘጋጀው የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር መድረክም ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውንና አማራጭ ሃሳባቸውን ለመራጩ ህዝብ እንዲያቀርቡ መደረጉን አብራርተዋል።

በመመሪያው መሰረትም ለፖለቲካ ፓርቲዎች የአየር ሰዓት ድልድል ተደርጎ ፓርቲዎች ሃሳቦቻቸውን ለህዝብ ተደራሽ እንዲሆን መደረጉንም ጠቅሰዋል።

የመራጮች ትምህርት ለሚሰጡ 169 ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቦርዱ ፈቃድ መስጠቱን ጠቁመው፤ ምርጫውን ለሚታዘቡ 55 የሀገር ውስጥ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንዲታዘቡ ፈቃድ መስጠቱንም ተናግረዋል።

ከአፍሪካ ህብረት 59 አባላት ያሉት ታዛቢዎች ቡድን መምጣቱን ገልጸው፤ ከኢጋድ ደግሞ 26 አባላት ያሉት ቡድን እንደሚታዘቡም አክለዋል።

ቦርዱ በጥቅሉ ለ68 መገናኛ ብዙሃን ምርጫውን እንዲዘግቡ ፈቃድ መስጠቱን ጠቁመው፤ ከዚሁ ወስጥ 56 የሀገር ውስጥ ሲሆኑ 12 ደግሞ የውጭ መገናኛ ብዙሃን መሆናቸውን ገልፀዋል።

የቁሳቁስ ስርጭቱ ቀድሞ በተያዘው መርሐ ግብር መሠረት በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው፤ የቁሳቁስ ስርጭቱ በተያዘለት ጊዜ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ የምርጫ ጣቢያዎችም ለምርጫው ሙሉ ዝግጅታቸውን እንደሚያጠናቅቁም ሰብሳቢዋ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም