በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ ለመስጠት ተዘጋጅተናል - ኢዜአ አማርኛ
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ ለመስጠት ተዘጋጅተናል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2018(ኢዜአ)፦ ሰኞ ግንቦት 24 ቀን በሚካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ይበጀናል ለሚሉት ፓርቲ ድምጻቸውን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም መራጮች ድምፅ የሚሰጡበት ቀን ነው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫ ቦርድ ባዘጋጀው መድረክ ለምርጫ ክርክሩ በ19 ዙር ያካሄደ ሲሆን፤ ክርክሩም በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ዲጂታል አማራጮች ለመራጩ ህዝብ ተደራሽ ተደርጓል።
የፊታችን ሰኞ በሚካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዙሪያ ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ ይበጀናል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ ዕለቷን በጉጉት እየተጠባበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል እሸቱ ያደታ፤ በምርጫ ወቅት የአንድ ሰው ድምፅ ለሀገር ግንባታና ለዴሞክራሲ ሥርዓት መጎልበት ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
ነገ ሀገርን የሚጠቅመውንና የሚመራውን ለይቶ መምረጥ የሚያስችላቸውን ዝግጅት እንዳጠናቀቁም ገልጸዋል።
ሌላኛዋ የመዲናዋ ነዋሪ አበራሽ ገብረመድህን በበኩላቸው፤ ፓርቲዎች ያደረጉትን የፖሊሲ አማራጭ ክርክሮችንና ፕሮግራሞችን በንቃት ሲከታተሉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
በዚህም ለኢትዮጵያና ህዘቦቿ ተጠቃሚነት ለሚሰራ ፓርቲ ድምፅ መስጠት የሚያስችል ግንዛቤ መያዛቸውንና በዕለቱም ድምጽ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
ምርጫ ለአንድ ሀገር የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ልምምድ መጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ያሉት ደግሞ ሌላኛው የመዲናዋ ነዋሪ ሀብታሙ ኪዳኔ ናቸው።
ለዚህም ለሀገር ዕድገትና ለህዝብ ተጠቃሚነት የተሻለ እንደሚሰራ እምነት የሚጥልበትን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ የወሰደችውና ቀኑን በጉጉት እየተጠባበቀች መሆኑን የገለጸችው ወጣት ባንቻየሁ በሪሁን፤ ሀገርን ለሚመራና ለሚያሻግር ድምፄን ለመስጠት ዝግጁ ነኝ ብላለች።
ሌላው ያነጋገርነው ወጣት አቤል ሀይሉ በበኩሉ፤ የምርጫ ካርድ አንድ ድምፅ የሀገርን መጻኢ ዕድል በመወሰን ረገድ ትልቅ ድርሻ ስላለው በፓርቲዎች ክርክር መነሻነት የሚበጀውን ፓርቲ ለመምረጥ በዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግሯል።
የአንድ ሰው ድምጽ ዋጋ ስላለው የወሰድኩትን የምርጫ ካርድ የምፈልገውን በመምረጥ የዜግነት ድርሻዬን ለመወጣት ተዘጋጅቻለሁ ያለችው ደግሞ ለምለም ዘለቀ ናት።
#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ #ENA