ቀጥታ፡

መራጩ ሕዝብ ሰላሙ ተጠብቆ ድምፁን እንዲሰጥ አስተማማኝ ዝግጅት ተደርጓል- የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2018(ኢዜአ)፦ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍፁም ሰላማዊ እና ስኬታማ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ፣ ከሌሎች  የፀጥታ አካላት ጋር በከፍተኛ ቅንጅት እና ቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ በክልሉ እያከናወነ ያለውን መጠነ-ሰፊ የሰላም ማስከበር ሥራ አስመልክቶ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ድሪባ መኮንን በሰጡት መግለጫ፣ የምርጫው የቅድመ-ዝግጅት ምዕራፍ ከተጀመረበት ጊዜ አንሥቶ ከክልሉ እና ከፌዴራል የፀጥታ መዋቅሮች የተወጣጣ የጋራ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ ቀጣይነት ያለው ሥራ በትኩረት ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ጠቅላላ ምርጫውን ለማደናቀፍ እና በሕዝብ ላይ ሁከት ለመፍጠር የተንቀሳቀሱ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን የመለየት እና ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ የመውሰድ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ባሻገር በተከናወነው የተቀናጀ እና በተደራጀ የፀጥታ ማስከበር ሥራ፣ ለምርጫው ሂደት ስኬታማነት እጅግ ወሳኝ የሆኑት የምርጫ ቁሳቁሶች ያለምንም የፀጥታ እንቅፋት እና መስተጓጎል በተፈለገው ቦታ እና ጊዜ በሰላም መሰራጨታቸውን ተናግረዋል።

የምርጫው ሂደት ፍፁም ሰላማዊ፣ ነጻ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የተጀመረው የፀጥታ ጥበቃ እና የክትትል ሥራ ምርጫው ተጠናቅቆ ውጤት እስኪገለጽ ድረስ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመላክቷል።

በመሆኑም የክልሉ ነዋሪዎች እና መራጮች በፍፁም ራስ መተማመን በምርጫው ዕለት በነቂስ ወጥተው ድምፃቸውን እንዲሰጡ ኮሚሽኑ ጥሪውን አቅርቧል።

በየአካባቢው በልዩ ሁኔታ የተደራጀው የጋራ የፀጥታ ግብረ-ኃይልም አጠቃላይ የምርጫው ሂደት እስኪጠናቀቅ ድረስ የሰላም እና የሕግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነቱን በትጋት እንደሚወጣ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም