የጤና ነገር - ኢዜአ አማርኛ
የጤና ነገር
በዮሐንስ ደርበው
በዓለም ላይ አሳሳቢ ደረጃ ከደረሱ የህመም ዓይነቶች አንዱ …
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ዶክተር ሞላወርቅ አየለ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በዓለምም ሆነ በሀገራችን ትኩረት ከሚሹ የህመም ዓይነቶች አንዱ ስለሆነው የደም ግፊት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በቆይታቸውም፤ ለደም ግፊት አጋላጭ ስለሆኑ ምክንያቶችና ሊደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄም እንዲሁም ከደም ግፊት መድሃኒት አወሳሰድ ጋር በተያያዘ ሳይንሳዊ ማብራሪያዎችን እና ምክረ ሐሳቦችን አቅርበዋል።
· የደም ግፊት ምንድን ነው?
ደም በደም ሥሮቻችን ሲያልፍ፤ የሚለካው መጠን “የደም ግፊት” እንደሚባል ዶክተር ሞላወርቅ ያስረዳሉ።
የላይኛው (ሲስቶሊክ ወይም ከፍተኛው) የደም ግፊት መጠን ልብ በምትኮማተርበት ጊዜ ደም ወደ ደም ሥር ሲረጭ የሚለካው መሆኑንም ይገልጻሉ።
የታችኛው (ዲያስቶሊክ ወይም ዝቅተኛው) የደም ግፊት መጠን ደግሞ ልብ ደም ለመቀበል ለአፍታ ዕረፍት በምታገኝበት ጊዜ የሚከሰት የግፊት ደረጃ መሆኑንም ይገልጻሉ።
· የደም ግፊት ደረጃዎች እና ማስጠንቀቂያቸው
ዶክተር ሞላወርቅ እንደሚሉት፤ የጤናማ ሰው የደም የግፊት መጠን 120 በ 80 እና በታች መሆን ይኖርበታል።
በሌላ በኩል ግን ይላሉ፤ የላይኛው ከ120 እስከ 129 የታችኛው ደግሞ ከ80 በታች ከሆነ “ከፍ ያለ ወይም የጨመረ የደም ግፊት ደረጃ” ይባላል።
የላይኛው ከ130 እስከ 139 ወይም የታችኛው ከ80 እስከ 90 ከሆነ ደግሞ “ደረጃ አንድ የደም ግፊት” እንደሚባል ያስረዳሉ።
የላይኛው ከ140 በላይ ሲሆን እና የታችኛው ከ90 በላይ ከሆነ ደግሞ “ደረጃ ሁለት የደም ግፊት” እንደሚባል ነው የሚገልጹት።
በሌላ በኩል “የከፋ የደም ግፊት ደረጃ” የሚባል እንዳለ ጠቁመው፤ ይህም የላይኛው ከ180 በላይ እና የታችኛው ከ120 በላይ ሲሆን ነው በማለት ያብራራሉ።
· ለደም ግፊት መጨመር መንስዔዎቹ ምንድን ናቸው?
በዋናነት ሁለት ዓይነት የደም ግፊት መኖሩን ያነሱት የሕክምና ባለሙያው፤ ከፍተኛ የደም ግፊት እና መንስዔው የሚታወቅ የደም ግፊት መሆኑን አስረድተዋል።
በዋናነት ወይም በአብዛኛው ከ90 እስከ 95 በመቶ የሚሆነው ከፍተኛ ደም ግፊት የሚባለው መሆኑን ገልጸው፤ በርካታ መንስዔዎች ሊኖሩት እንደሚችሉ ቢገመትም ሁሉም በውል እንደማይታወቁ ያነሳሉ።
ከበርካታ መንስዔዎቹ መካከልም፤ በቤተሰብ የሚወረስ (ተላላፊ)፣ አካባቢያዊ ምክንያቶች እንዲሁም የአኗኗር ዘይቤ የሚሉት እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።
የአኗኗር ዘይቤ ሲባልም፤ የአመጋገብ ሥርዓት በተለይም ጨው የበዛበት ምግብ፣ ክብደት መጨመር፣ አካባቢያዊ ሁኔታዎች (አልኮል መጠጣት፣ ሲጋራ ማጨስ)፣ የስኳር ታማሚ መሆን የሚሉት ይጠቀሳሉ ይላሉ።
· ለደም ግፊት በተለይም እነማን ተጋላጭ ናቸው?
ዕድሜ በጨመረ ቁጥር የደም ግፊት የመከሰት ዕድሉም እንደሚጨምር ጠቅሰው፤ በዚህም መሠረት ባብዛኛው ዕድሜያቸው ከፍ ያሉ ሰዎች ተጋላጭ መሆናቸውን ይናገራሉ።
እንዲም በቤተሰብ የደም ግፊት ኬዝ ያለባቸው ሰዎች፣ የማንነት ሁኔታ (ኢትኒክ ግሩፕ) ለምሳሌ፡- በጥቁሮች (አፍሪካውያን)፣ በኤስያውያን፣ በደቡብ ኤስያውያን ላይ ከፍተኛ የደም ግፊት ሊከሰት እንደሚችል ይገልጻሉ።
እንደ ዶክተር ሞላወርቅ ማብራሪያ፤ በአጠቃላይ አጋላጭ ምክንያቶች በሁለት ተከፍለው ሊታዩ ይችላሉ።
አንደኛው፡- ልንከላከላቸው (ልንቀንሳቸው) የምንችላቸው መሆናቸውን በመግለጽ ይህም የአመጋገብ ሥርዓትን ማስተካከል፣ ክብደት መቀነስ፣ አልኮልና ሲጋራ ማቆም እና መሰል መሆናቸውን አብራርተዋል።
ሁለተኛው፡- ልንከላከላቸው የማንችላቸው መሆናቸውን ገልጸው ይህም፤ የዕድሜ መጨመር፣ የማንነት ሁኔታ (ኢትኒሲቲ) እና በቤተሰብ የሚተላለፍ የሚሉትን ጠቅሰዋል።
· የደም ግፊትን አስቀድሞ መከላከል ይቻላል?
የደም ግፊ ከተከሰተ መቆጣጠር እንጅ ማዳን እንደማይቻል ገልጸው፤ ከላይ እንደተጠቀሰው አስቀድሞ መከላከል ወይም ማዘግየት የሚቻል እና መከላከል የማይቻል የደም ግፊት ደረጃ መኖሩን አስረድተዋል።
· የደም ግፊት በውል የሚታወቅ ምልክት አለው?
የደም ግፊት ሲከሰት ምልክት እንደሌለው በማንሳት፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ “ዝምተኛው ገዳይ” እስከመባል መድረሱን ዶክተር ሞላወርቅ ያነሳሉ።
ግፊቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ግን፤ በአንድ ወይም በሁለት የሰውነት አካል ላይ ችግር ሊደርስ እንደሚችል ከዚህም ሲያልፍ እስከ ሞት እንደሚያደርስ ይጠቅሳሉ።
በተያያዘም፤ የራስ ምታት፣ የዐይን ብዥ ብዥ ማለት፣ ትንፋሽ ማጠር፣ የድካም ስሜት፣ አንገት የመያዝ ዓይነት ስሜቶች የደም ግፊቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ሊስተዋሉ የሚችሉ መሆናቸውን አብራርተዋል።
አክለውም፤ በአብዛኛው በሕብረተሰቡ ላይ የደም ግፊት ምልክት ሳያሳይ ከፍተኛ ደረጃ ይደርስና ድንገት በጨመረ ጊዜ፤ ለሞት፣ ለአደጋ፣ ለልብ ድካም፣ አጣዳፊ ለሆነ የልብ ህመም፣ በጭንቅላት ላይ የደም መፍሰስ፣ የኩላሊት ድክመት፣ በደም ሥሮች በአግባቡ ደም እንዳይተላለፍ ማድረግ፣ ለዐይነ ስውርነት መዳረግን ጨምሮ መሰል ጉዳቶችን ሊያስከትል እንደሚችል አስገንዝበዋል።
· መድኃኒት አወሳሰድ ላይ መደረግ ያለበት ጥንቃቄ
ዶክተር ሞላወርቅ እንደገለጹት፤ አንድ ሰው ደም ግፊት እንዳለበት ከተነገረው በኋላ ሕክምናውም እንደ ደም ግፊቱ ደረጃ ይለያያል።
ይህንም በምሳሌ ሲያስረዱ፤ የላይኛው ከ120 እስከ 129 ከሆነ “የጨመረ ግፊት” ይባላል፤ እዚህ ላይ ሰውየው ጥንቃቄ እንዲያደርግ፣ አመጋገቡን እንዲያስተካክል፣ ስፖርት እንዲሠራ፣ ክብደት እንዲቀንስ፣ ሱስ (ሲጋራ፣ አልኮል) እንዲቀንስ ክትትል ይደረጋል ብለዋል። ስለዚህ መድኃኒት ሳይጀምር የአኗኗር ዘይቤን በማስተካከል የደም ግፊቱን ሊቀንሰው (ሊቆጣጠረው) ይችላል ማለት ነው ሲሉም ይገልጻሉ።
“ደረጃ አንድ ግፊት” የሚለው ላይ ከደረሱ ግን ሕክምና የሚጀምሩም የማይጀምሩም እንዳሉ ተናግረዋል። ይህም ማለት የላይኛው ከ130 እስከ 139 የታችኛው ከ80 እስከ 90 ከደረሰ ሕክምና የሚጀምሩት የስኳር ህመም ያለባቸው፣ የስትሮክ ህመም ያለባቸው፣ ከልብና ደም ሥር የተገናኙ ህመሞች ያሉባቸው ከሆኑ ቢያንስ አንድ የግፊት መድኃኒት መጀመርና ክትትል ማድረግ አለባቸው ይላሉ።
በሌላ በኩል ግን ይላሉ ዶክተር ሞላወርቅ፤ ሰዎች “ደረጃ ሁለት ግፊት” ላይ ከደረሱ (የላይኛው ከ140 የታችኛው ከ90 በላይ ከሆነ) ሁሉም መድኃኒት መጀመር እንዳለባቸው በአጽንዖት ገልጸዋል። የሚጀምሩት መድኃኒትም አሁን ባለው በተሻሻለው የሕክምና ዘይቤ ሁለት መድኃኒቶች የሚጀምሩበት ሁኔታ እንዳለ ነው የሚያስረዱት።
የአኗኗር ዘይቤን ማስተካከል ግን ለሁሉም የግፊት ዓይነቶች መሠረት (የሚመከር) መሆኑን አስገንዝበዋል። ስለዚህ መድኃኒት ጀምሬያለሁ ብሎ የአኗኗር ዘይቤው ላይ ቸልተኝነት ሊኖር እንደማይገባም ነው የሚመከሩት።
በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከግፊት ጋር በተያያዘ ወደ ሆስፒታል መጥተው የሚታከሙ ታካሚዎች አብዛኞቹ፤ ጀምረው ያቋረጡ፣ ለመጀመር ፍላጎት የሌላቸው፣ ቅድመ ምርመራ ባለማድረግ ምክንያት ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ የተጎዱ ናቸው ሲሉ አብራርተዋል። ስለዚህ የግፊት መድኃኒት ከተጀመረ ሊቋረጥ እንደማይችል አስጠንቅቀዋል። በየጊዜው ክትትል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም አክለዋል። በሂደት እንደ ግፊቱ ሁኔታ መድኃኒቶች ሊቀነሱም ሊጨመሩም እንደሚችሉ አመላክተዋል።
· የመስፋፋት ደረጃ የዓለም ጤና ድርጅት በ2024 ያወጣውን መረጃ ዋቢ አድርገው፤ 1/3ኛው የዓለም ሕዝቦች በደም ግፊት እንደሚጠቁ ዶክተር ሞላወርቅ አንስተዋል።
ከእነዚህ መካከልም፤ 7 ነጥብ 6 ሚሊየን ገደማው በአንድም በሌላም ምክንያት ከደም ግፊት ጋር በተያያዘ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ጠቁመዋል።
አብዛኞቹ የደም ግፊት ታማሚዎች ቁጥር የሚመዘገበው ደግሞ በመካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ሀገራችንን ያካትታል ሲሉ ገልጸዋል።
በሀገራችን ደረጃም ይላሉ ዶክተር ሞላወርቅ፤ የቅርብ ጊዜ መረጃዎች ባይኖሩም ከግፊት ጋር በተያያዘ በ2001 ላይ በ35 ሳይቶች የተጠኑ ጥናቶች ውጤቶች እንደሚያመላክቱት ከ21 እስከ 25 በመቶ ያህሉ ሕዝብ በደም ግፊት የሚጠቃ ነው ይላሉ።
በአብዛኛው ደግሞ ከተማ ላይ እንደሚበዛ ጠቁመው፤ በተለይም አዲስ አበባ ላይ እስከ 30 በመቶ እንደሚደርስ የጥናቶቹ ውጤቶች ማመላከታቸውን ተናግረዋል።
አብዛኞቹ ኬዞች ደግሞ ዕድሜያቸው ከፍ ያለ፣ ክብደታቸው የጨመረ፣ አልኮል እና ሲጋራ የሚጠቀሙ እና የስኳር ህመም ያለባቸው ሰዎች ጋር የሚገናኙ መሆናቸውን አስረድተዋል።
እንደ ዓለም አቀፍ ደረጃም ኬዙ ካለባቸው መካከል ግማሽ ያህሉ ግፊት እንዳለባቸው እንኳን እንደማያውቁ ነው የሚገልጹት።
ለግፊት ሕክምና ትክክለኛ ክትትል አድርገው ግፊታቸውን በአግባቡ የሚቆጣጠሩት ከ 5 ሰዎች 1 መሆኑንም ጥናቶች ያሳያሉ ብለዋል።
· ምክረ ሐሳብ
በሀገራችን በሕብረተሰቡ ዘንድ ለደም ግፊት መለካት ኬዙ ከተገኘም የሕክምና ክትትል የማድረግ ሁኔታዎች ዝቅተኛ መሆናቸውን አንስተዋል።
ስለዚህ ሕብረተሰቡ የደም ግፊት ምልክት ሳያሳይ ከአካል ጉዳት እስከ ሞት ሊያደርስ እንደሚችል ተገንዝቦ፤ የደም ግፊቱን የመለካት ልምምዱን ሊያዳብር እንደሚገባ ዶክተር ሞላወርቅ መክረዋል።
በሌላ በኩል እንደ ሀገራችን ባሉ ሆስፒታሎች በጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ ወይም መቋረጥ (ስትሮክ) ካለባቸው ሰዎች ከ70 እስከ 85 በመቶው ከደም ግፊት ጋር በተያያዘ የሚከሰት መሆኑን ገልጸው፤ ድንገተኛ ግፊት መጨመር ከልብ እና ከደም ሥሮች ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ጉዳት እያመጣ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በዓለምም ሆነ እንደ ሀገር አሳሳቢ ደረጃ ከደረሱ የህመም ዓይነቶች አንደኛው ግፊት መሆኑንም አረጋግጠዋል።
ስለዚህ የደም ግፊትን መለካት፣ የአኗኗር ዘይቤን ማስተካከል፣ ከሱስ መራቅ፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማዘውተር ለጤናማ ሕይወት ከፍተኛ ሚና እንዳለው መክረዋል።
#የጤና ነገር #ኢዜአ #የደም_ግፊት