ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ስኬት ዜጎች ጤናማ ህይወት የሚመሩበትን አስቻይ ምኅዳር እየፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ስኬት ዜጎች ጤናማ ህይወት የሚመሩበትን አስቻይ ምኅዳር እየፈጠረ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

የኢትዮጵያ አካባቢ ጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች ማኅበር 8ኛውን ዓመታዊ የሳይንሳዊ የምርምር ኮንፍረንስ ''ለተሻለች ፕላኔት ጤና፤ ዘመናዊና መቋቋም የሚችሉ የውሃ፣ ሳኒቴሽንና ሃይጅን ቴክኖሎጂዎች'' በሚል መሪ ሀሳብ እያካሄደ ይገኛል።


 

በጤና ሚኒስቴር የማህበረሰብ ተሳትፎና የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ መሪ ሥራ አስፈፃሚ እስራኤል አታሮ በመድረኩ፤ የአካባቢ ጥበቃ ጤናማ ዜጋና ማህበረሰብ ለመገንባት ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።

ለዚህም ዜጎች የሚጠቀሟቸውን የውሃ፣ የአየርና የአካባቢ ሥነ-ምኅዳራዊ ጤናማነትና ደኅንነት መጠበቅ እንደሚያስፍልግ ገልጸዋል።

የአካባቢ ጤንነትን ለመጠበቅ የሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር ውጤታማነትን በማሳደግ የቴክኖሎጂ አቅምን ማጎልበት እንደሚገባ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የስኬት ጉዞ ዜጎች ጤናማ ህይወት የሚመሩበትን አስቻይ ምኅዳር እየፈጠረ መሆኑን አንስተዋል።

ማኅበሩ በሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በማመስገን፤ የውሃ፣ ሳኒቴሽንና ሃይጅን ሥርዓትን ለማዘመን በሚከናወኑ ተግባራት የዘርፉ ተዋናዮች ገንቢ ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።


 

​የኢትዮጵያ አካባቢ ጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር አርጋው አምበሉ በበኩላቸው፤ የተሻለ የመኖሪያ ከባቢና ንፅህና የዜጎች ምርጫ ሳይሆን ጤናን የመጠበቅ ግዴታ ነው ብለዋል።

ለዚህም የውሀ የሳኔቴሽንና የሃይጅን አገልግሎቶች ውጤታማ የሚሆኑባቸውን ቴክኖሎጂዎች ማፍለቅና ወደ ተግባር መቀየር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።


 

የውሃ፣ ሳኒቴሽንና ሃይጅን አገልግሎት ለዜጎች አስፈላጊና መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸው ያሉት ደግሞ የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ተወካይ ተመስገን ሳሙኤል ናቸው።

የኢትዮጵያን የውሃ፣ ሳኒቴሽንና ሃይጅን አገልግሎት በቴክኖሎጂ ለማዘመን በሚደረገው ጥረት ከመንግስት ጋር በትብብር እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

የክርስቲያን እፎይታና ልማት ማኅበራት ኮንሶርቲየም በኢትዮጵያ ተወካይ በርሄ ፍሰሀ በበኩላቸው፤ ጤናማና ደኅንነቱ የተጠበቀ አካባቤ የዜጎችን ጤንነት ለመጠበቅ ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።

በጉባኤው ለአካባቢ ጤና መጠበቅ ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና እና ዕውቅና ተበርክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም