ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የሀሳብ ልዩነትን በሰለጠነ ምክክር መፍትሔ በመስጠት ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር የሚያስችል ጠንካራ መሠረት እየተጣለ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የሀሳብ ልዩነትን በሰለጠነ ምክክር መፍትሔ በመስጠት ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር የሚያስችል ጠንካራ መሠረት እየተጣለ መሆኑን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገለፁ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በዋና ዋና ክንውኖቹ፣ አሁን የደረሰበትን ደረጃና በቀሪ ሥራዎች ዙሪያ ከቲንክ ታንክ፣ የግልና የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን ጋር ውይይት እያካሄደ ይገኛል።

ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በዚሁ በመድረኩ፤ ኮሚሽኑ የሃሳብ ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ ማስኬድ የሚያስችል ተቋም ሆኖ መገንባቱን ገልጸዋል።

በዚህም እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባትን ለመፍጠር የሰለጠነ የምክክር አውድ በመዘርጋት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በምክክር ሂደቱም በወረዳ ደረጃ በተካሄዱ የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረኮች የነበረው ተሳትፎ 93 ከመቶ መሆኑ የአጀንዳ ማሰባስብና ተሳታፊ ልየታ ሂደቱን አሳታፊና አካታችነት እንደሚያሳይ አንስተዋል።

በምክክር መድረኮቹም የመምህራን ማኅበር፣ ዕድሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የኃይማኖት ተቋማትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ዳኞች፣ የወረዳ አስተዳደር ተወካዮችና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሳተፋቸውን አስገንዝበዋል።

ታላላቅ ህዝባዊ የምክክር መድረኮችን በመፍጠር ኮሚሽኑ በቀጥታ አጀንዳዎችን የማሰባሰብና ተሳታፊ የመለየት ሥራ መሰራቱን አስረድተዋል።

በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚኖሩ ዜጎችን ለማሳተፍ በደቡብ አፍሪካ፣ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች፣ ስዊድንና እንግሊዝ የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ ክርክሮች መካሄዳቸውን ተናግረዋል።

የእስካሁኑ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት በየደረጃው መግባባት ላይ ለመድረስና ለቀጣይ ሀገራዊ ምክክር ጠንካራ መሰረት መጣል መቻሉ አንስተዋል።

በቀጣይም ዋናው የምክክር ጉባኤ ለማካሄድ አስፈላጊ ዝግጅቶች እየተደረጉ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም