በጭሮ አንድ እና በነገሌ ምርጫ ክልል ለድምፅ መስጫ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች እየተሰራጩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጭሮ አንድ እና በነገሌ ምርጫ ክልል ለድምፅ መስጫ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች እየተሰራጩ ነው
ነገሌ ቦረና/ጭሮ፤ ግንቦት 21/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በጭሮ አንድ እና በነገሌ ምርጫ ክልል ለድምፅ መስጫ የሚያገለግሉ የምርጫ ቁሳቁሶች እየተሰራጩ መሆኑን የምርጫ ክልሎቹ አስተባባሪዎች ገለጹ።
በጭሮ አንድ ምርጫ ክልል ስር ለሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለድምፅ መስጫ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን የማሟላት ስራ መጠናቀቁን የምርጫ ክልሉ አስታውቋል።
የምርጫ ክልሉ አስተባባሪ አቶ መሐመድ ቡሹራ እንደገለፁት በጭሮ ወረዳና ጭሮ ከተማ 120 የምርጫ ጣቢያዎች ለድምፅ መስጫ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች ሙሉ በሙሉ ተዳርሷል።
በምርጫ ክልሉ ስር በተደራጁ የምርጫ ጣቢያዎች ተገቢውን ስልጠና የወሰዱ 720 የምርጫ አስፈፃሚዎች መመደባቸውም ገልፀዋል።
የምርጫ ጣቢያዎቹ ለድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ምቹና የተሟሉ በመሆናቸው በዕለቱ ከማለዳው 12:00 ሰዓት የድምፅ መስጠት ሂደቱ ይጀመራል ብለዋል።
በተመሳሳይ በነገሌ ምርጫ ክልል ወደ የምርጫ ጣቢያው ቁሳቁስ እየደረሰ መሆኑን የምርጫ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ገልጿል።
የምርጫ ክልሉ አስተባባሪ አቶ አባይነህ ወርቁ ከማዕከል ወደ ነገሌ ምርጫ ክልል አስፈላጊው የምርጫ ቁሳቁስ ገብቶ፣ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ከትናንት ጀምሮ እየተሰራጨ ነው ብለዋል።
በዞኑ 5 ወረዳዎች በሚገኙት 167 የምርጫ ጣቢያዎች ቁሳቁስ እየደረሰ መሆኑን ገልጸው፤ ለሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ዛሬና ነገ ሙሉ በሙሉ እንደሚደርስም ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በአምቦ አንድ ምርጫ ክልል ስር ለሚገኙ 105 የምርጫ ጣቢያዎች አስፈላጊው ግብዓት እየተሰራጨ መሆኑን የምርጫ ክልሉ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ምስጋና ሳደሳ ገልጸዋል።
የምርጫ ክልሉ በአምቦ ከተማና በአምቦ ወረዳ የሚገኝ ሲሆን የድምፅ መስጫ ቁሳቁስ ስርጭቱ በእቅዱ መሰረት እየተከናወነ መሆኑንም አክለዋል።
እየተሰራጩ ካሉ ቁሳቁሶች መካከል የድምፅ መስጫ ወረቀቶች፣ የድምፅ መስጫ ሳጥኖች እና ሌሎች ለምርጫው ቀን የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ይገኙበታል ብለዋል።