ቀጥታ፡

በዝናብ የተቋረጠው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ ነገ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንዲቀጥል ተወሰነ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ34ኛ ሳምንት መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ስታዲየም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በኢትዮ ኤሌክትሪክ መካከል እየተካሄደ የነበረው ጨዋታ በከባድ ዝናብ ምክንያት ተቋርጧል።

ጨዋታው በ34ኛው ደቂቃ ላይ በስታዲየሙ ላይ በጣለው ከባድ ዝናብና ሜዳው ውኃ በመቋጠሩ ምክንያት ሊቋረጥ እንደቻለ የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።

ይህን ተከትሎ የተቋረጠው ጨዋታ ነገ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ከ30 አንስቶ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ከቆመበት ደቂቃ ጀምሮ እንደሚቀጥል ታውቋል።

ጨዋታው እስከተቋረጠበት ደቂቃ ድረስም ሁለቱም ቡድኖች ግብ ሳያስቆጥሩ በባዶ ለባዶ ውጤት ላይ ነበሩ።

በሌላ በኩል ዛሬ 10 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ሊደረግ ታስቦ የነበረው እና በዝናብ ምክንያት ያልተካሄደው የወላይታ ድቻ እና የነገሌ አርሲ የ34ኛ ሳምንት ጨዋታ ሐሙስ ግንቦት 27 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንዲደረግ መወሰኑን ማህበሩ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም