ቀጥታ፡

የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የክርክር መድረክ የፓርቲዎች ተሳትፎ ጎልቶ የታየበት ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2018(ኢዜአ)፦ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የክርክር መድረክ የፓርቲዎች ተሳትፎ ጎልቶ የታየበት እንደነበረ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ ነዋይ ገለጹ።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም መራጮች ድምፅ የሚሰጡበት ቀን ነው።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫ ቦርድ ባዘጋጀው መድረክ ለምርጫ ክርክሩ በ19 ዙር ያካሄዱ ሲሆን፤ ክርክሩም በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ዲጂታል ሚዲያ አማራጮች ለመራጩ ህዝብ ተደራሽ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር ማጠናቀቂያ እና የጥሞና ጊዜ ማብሰሪያ መርሃ ግብር አካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራር አባላት፣የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ጨምሮ የመገናኛ ብዙኃን ተወካዮች ተገኝተዋል።

የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ ነዋይ በዚሁ ወቅት፤ ቦርዱ የምርጫ ሂደት ውጤታማነትን ማስጠበቅ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መስራቱን ገልጸዋል።

ቦርዱ ለመጀመሪያ ጊዜ ባዘጋጀው የፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክር መድረክም የፓርቲዎች የጎላ ተሳትፎ የተንጸባረቀበት እንደነበር ተናግረዋል።

የክርክር መድረኩ ፓርቲዎች በሃሳብ የበላይነት የተመሰረተ ጭብጥ ተኮር ክርክር በማድረግ በሞዴልነት የሚወሰድ መሆኑንም አብራርተዋል።

በዚህም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጭ ሃሳባቸውን በሰለጠነ አግባብ ለመራጩ ህዝብ በቀጥታ በማስተላለፋቸው መራጩ ህዝብ ግንዛቤ መያዙን አንስተዋል።

የክርክር ሂደቱን በስኬት ለማከናወን በተደረገው ዝግጅት ገለልተኛ ሙያተኞች፣ አስተባባሪዎች፣ ምሁራንና ተባባሪ አካላት በአቅም ግንባታ ስልጠና መሳተፋቸውን ጠቅሰዋል።

የተለያዩ የመገናኛ ብዙኅን ሙያተኞች በሂደቱ መሳተፋቸውም ትልቅ የስኬት ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።

በክርክር ሂደቱ ብዝኅነትና ሕብረ ብሔራዊነትን በሚያንፀባርቅ መልኩ አማርኛን ጨምሮ በተለያዩ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች እንዲተላለፍ በማድረግ ስኬታማ ስራ መሰራቱን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም