የኢትዮጵያ ከተሞች የመሬት ይዞታ ካዳስተር ምዝገባ ሥርዓት የገቢ አቅማቸውን በማሳደግ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከተሞች የመሬት ይዞታ ካዳስተር ምዝገባ ሥርዓት የገቢ አቅማቸውን በማሳደግ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ነው
አዲስ አበባ፤ግንቦት 21/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ከተሞች የመሬት ይዞታ ካዳስተር ምዝገባ ሥርዓት የከተሞችን የገቢ አቅም በማሳደግ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፈንታ ደጀን ገለጹ።
ከተሞች የገቢ አቅማቸውን በመጠቀም ብድር ማግኘት የሚችሉበትን ሥርዓት ለመዘርጋት እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ደጀን ለኢዜአ እንዳሉት፤ ከተሞች ለአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ናቸው።
የኢትዮጵያ ከተሞች እስከ 58 በመቶ ለአጠቃላይ ሀገራዊ የምርት ድርሻ እያበረከቱ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በኮሪደር፣ወንዝ ዳርቻና ዲጂታላይዜሽን የተከናወኑ ስኬታማ የልማት ተግባራት ስሉጥ ከተሞችን በመፍጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።
ዘመናዊ የከተሜነት ምኅዳር የመፍጠር ሥራም ዜጎች ፈጣንና ቀልጣፋ የመንግሥት አገልግሎት የሚያገኙበት አስቻይ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑን አንሰተዋል።
የከተሞች ማዘጋጃ ቤታዊና የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ወደ ዲጂታል ሥርዓት መሸጋገሩም ፈጣንና ቀልጣፋ ምኅዳር መፍጠሩን አስረድተዋል።
በተለይም በአንድ ማዕከል አገልግሎት ዜጎች የመንግሥት አገልግሎቶችን በተማከለ ሥርዓት በጥራትና ፍጥነት የሚያገኙበት ዕድል እንደፈጠረ ተናግረዋል።
የከተሞችን የመሬት ይዞታ በፍትሐዊነት ለማስተዳደርም ምዝገባ እየተካሄደ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ 6 ነጥብ 6 ሚሊየን ፐርስል የከተማ መሬት ውስጥ 33 በመቶው ባለፉት ሶስት ዓመታት መመዝገቡን ጠቅሰው፤ በካዳስተር ስርዓት መሬትን የማስተዳደር ስራ በስፋት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለአብነትም የአዳማ ከተማን ጨምሮ ሌሎች ከተሞች የመሬት ምዝገባ ማጠናቀቃቸው አብራርተዋል።
የከተሞችን ሃብትና ገቢ የማመንጨት አቅም ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራትም ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
በዚህም አሁን ላይ የከተሞች ገቢ ከአራት ዓመታት በፊት ከነበረበት 10 ቢሊዮን ብር ወደ 80 ቢሊየን ብር ማድረስ እንደተቻለ ገልጸዋል።
ይህም የከተሞችን ገቢ የመሰብሰብ አቅም በማሳደግ በሚያመነጩት ገቢ መጠን በመጠቀም ብድር የሚያገኙበት ሥርዓት እየተዘረጋ መሆኑን ተናግረዋል።