ቀጥታ፡

ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጭ ሃሳባቸውን ለህዝብ ማስተዋወቅ የቻሉበትን መድረክ በመፍጠር ተጨባጭ ተግባራት ተከናውነዋል

አዲስ አበባ፤ግንቦት 21/2018(ኢዜአ)፦በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጭ ሃሳባቸውን ለህዝብ ማስተዋወቅ የቻሉበትን መድረክ በመፍጠር በኩል ተጨባጭ ተግባራት መከናወናቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሀይሉ ገለጹ።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም መራጮች ድምፅ የሚሰጡበት ቀን ጥቂት ቀናት ቀርተውታል።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫውም 47 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአጠቃላይ 10 ሺህ 934 ዕጩዎችን በማስመዝገብ በመገናኛ ብዙኅን አማካኝነት የፖሊሲ አማራጭ ሃሳቦቻቸውን ለህዝብ በስፋት የማስተዋወቅ ስራ ተሰርቷል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫ ቦርድ ባዘጋጀው መድረክ ለምርጫ ክርክሩ በ19 ዙር ያካሄዱ ሲሆን፤ክርክሩም በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ዲጂታል አማራጮች ለመራጩ ህዝብ ተደራሽ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሀይሉ፤በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጭ ሃሳባቸውን ለህዝብ ማስተዋወቅ የቻሉበትን መድረክ መፍጠር እንደተቻለ ገልጸዋል።

መራጩ ህዝብም በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ድምፅ በመስጠት ወኪሎቹን እንዲመርጥ ለማስቻል የምርጫ ቅስቀሳና ክርክር ክህሎት ማዳበሪያ የተግባር ልምምድ ስልጠና መሰጠቱን አስታውሰዋል።

በፖሊሲ ጥናት ምሁራንና ሙያተኞች በመታገዝ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አማራጭ ሃሳብ ልዩነትና ተመሳሳይነት የሚለካበትን መረጃ የመሰብሰብ ሥራ በጥንቃቄ መሰራቱን ተናግረዋል።

የክርክር ሂደቱን ቅርፅ ውጤታማነት ለማስጠበቅ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽ ሙያተኞች የተሳተፉበት ተከታታይ ውይይት በማድረግ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከተለምዷዊ ክርክር ወጣ ያለ ክርክር አካሂደዋል ብለዋል።

የክርክር ሂደቱ ተጋባዥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችና ገለልተኛ ተቋማት ወኪሎችም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ጥያቄ የሚያቀርቡበት ዕድል እንደተፈጠረ አንስተዋል።

በዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከታዳሚ በሚቀርብላቸው ጥያቄ የህዝብን ፍላጎት በመረዳት መለካት የሚችሉበትን የክርክር ቅርፅ መስጠት እንደተቻለ አብራርተዋል።

የክርክር መሪዎችም ረጅም ጊዜ በሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን የሰሩና ገለልተኝነታቸውን ለማረጋገጥ ለፓርቲዎች በመላክ አስተያየት እንዲሰጡበት መደረጉን ጠቅሰዋል።

የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ፖሊሲና የፕሮግራም ዓላማ ለህዝብ በግልፅ በማስተዋወቅ መራጮች በቂ ግንዛቤ የሚያገኙበትን ዕድል መፈጠሩን አስረድተዋል።

በምርጫ ሂደቱ የጥሞና ጊዜም ዜጎች በየቤታቸው ለማን ድምፅ መስጠት እንዳለባቸው ሃሳብ የሚያሰላስሉበትና ፓርቲዎችም ዕጩዎች ያለውን ድባብ የሚከታተሉበት መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ሂደቱን ነጻ፣ ፍትሐዊ፣ ተዓማኒ፣ ገለልተኛ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አበክሮ እየሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል።

በግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ከጥዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በሚካሄደው ምርጫም የአፍሪካ ሕብረት፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) እና የሀገር ውስጥ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በታዛቢነት እንደሚታደሙ አስታውቀዋል።

የምርጫ ሂደቱን ለመጎብኘት ጥያቄ ያቀረቡ 16 የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላትንም ምላሽ ለመስጠት በሂደት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም