ቀጥታ፡

የአቮካዶን ምርታማነት በማሳደግ ከዘርፉ የሚገኘውን ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ለማሻሻል እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ግንቦት 21/2018(ኢዜአ)፦ የአቮካዶን ምርታማነት በማሳደግ ከዘርፉ የሚገኘውን ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደሳለኝ ተሻለ ገለጹ፡፡

በግብርና ሚኒስቴር አዘጋጅነት በብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም ዙሪያ የዘርፉን ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደሳለኝ ተሻለ እንዳሉት፤ የአቮካዶ ምርት በአገር ደረጃ ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው የግብርና ምርት ኢኒሼቲቮች ውስጥ አንዱ ሲሆን፣ ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግ ረገድ ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

ይህ ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም በአገሪቱ እያደገ የመጣውን የፍራፍሬ ፍላጎት ለማሟላትና የኢትዮጵያን የኤክስፖርት አቅምን ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል።

የአቮካዶ ምርት ለተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉትም አብራርተዋል።

ሚኒስቴሩ አገር አቀፍ የአቮካዶ ልማትን ይበልጥ ለማስፋፋት፣ ምርታማነትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገርና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ የዘርፉን ተዋናዮች፣ አምራቾችና ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ በቅንጅት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም መሠረት ከፍተኛ ምርት የሚሰጡና የተለያዩ በሽታዎችን የሚቋቋሙ ተመራጭ የአቮካዶ ዝርያዎች ለአርሶ አደሮች ተሰራጭተው ከፍተኛ ውጤት እያስገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አነስተኛ አምራች አርሶ አደሮችን በክላስተር በማደራጀት፣ ዘመናዊ የኩሬ አጠቃቀምና የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂ ስልጠናዎችን በመስጠት የምርት ጥራትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ማድረግ የሚያስችል አሠራር እየተዘረጋ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህም አርሶ አደሩን በቀጥታ ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር ለማስተሳሰር ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

ይህ ብሔራዊ ፕሮግራም የአርሶ አደሩን የኑሮ ዘይቤና ገቢ ከመቀየር ባለፈ፣ በግብርናው ዘርፍ የሚገኘውን የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ገቢ በከፍተኛ መጠን ለማሳደግ የተቀረጸ ስትራቴጂካዊ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም