በደቡብ ኦሞ ዞን በዘንድሮው የበልግ እርሻ ለገበያ ተኮር ሰብሎች ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኦሞ ዞን በዘንድሮው የበልግ እርሻ ለገበያ ተኮር ሰብሎች ትኩረት ተሰጥቷል
ጂንካ፤ግንቦት 21/2018(ኢዜአ):- በደቡብ ኦሞ ዞን በዘንድሮ የበልግ እርሻ ለገበያ ተኮር ሰብሎች ትኩረት በመስጠት መሰራቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
የደቡብ ኦሞ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ምንላርገው አዲሱ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በዞኑ በዘንድሮ የበልግ እርሻ 108 ሺህ ሄክታር መሬት መልማቱን ገልጸዋል።
አጠቃላይ ከለማው መሬት ወደ 4 ሚሊዮን የሚጠጋ ምርት ለማግኘት እንደታቀደም ጠቅሰዋል።
በዘንድሮ የበልግ እርሻ ለገበያ ተኮር እና የኢንዱስትሪ ግብዓት ለሚሆኑ ስንዴ፣ ሰሊጥ፣ ካሳቫ እና ማሾ ሰብሎች ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል አርሶና አርብቶ አደሩ ውስን ሰብሎችን ብቻ በማልማት ለገበያ የሚያቀርብበትን ሁኔታ በመቀየር ገበያ ተኮር የሆነ አመራረት በመከተል በኩታ ገጠም በስፋት የሚያለሙበት ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።
ከዚህም ባሻገር አርሶና አርብቶ አደሩ በአካባቢው ያልተለመዱ እንደ ሩዝ እና ካሳቫ ምርቶችን ማምረት መጀመራቸውን አንስተው፥ በዚህም የገቢ አቅማቸው እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
በዞኑ ሳላማጎ ወረዳ ገሮ ቀበሌ በካሳቫ ምርት የተሰማሩት አርሶ አደር አለሙ ላስታ፥ በዘንድሮ የበልግ አዝመራ 17 ሄክታር መሬት ላይ ካሳቫ እያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል ።
መንግስት የእርሻ መሬት እና የእርሻ ትራክተር በማቅረብ እገዛ እያደረገላቸው መሆኑን ገልፀው፥ የግብርና ባለሙያዎችም ገበያ ተኮር የሆኑ ሰብሎችን እንዲያለሙ ሙያዊ ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ካሳቫ በአንድ ሄክታር እስከ 300 ኩንታል ምርት የሚያስገኝ እና ቶሎ የሚደርስ ሰብል መሆኑ ደግሞ ይበልጥ ተመራጭ አድርጎታል ነው ያሉት አርሶ አደሩ።
ሌላው የወረዳው አርሶ አደር አድማሱ ጩሉ፥ በዘንድሮ የበልግ አዝመራ በኩታ ገጠም 8 ሄክታር መሬት ላይ ሩዝ እያለሙ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ሩዝ ውሃ በሚተኛባቸው ረግረጋማ ቦታዎች ምርት የሚሰጥ በመሆኑ ሩዝ እያለሙ መሆኑን ገልጸዋል።
በአካባቢው ቀደም ሲል በቆሎ እና ማሽላ በስፋት የማልማት ልምድ እንደነበር ጠቁመው፥ አሁን ላይ በመንግሥት ድጋፍ ገበያ ተኮር የሆኑ ሰብሎችን በማልማት የተሻለ ገቢ ማግኘት መጀመራቸውን ገልጸዋል።