የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ34ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን መርሐ ግብር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ34ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን መርሐ ግብር
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 34ኛ ሳምንት ዛሬ አራት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ወላይታ ድቻ ከነገሌ አርሲ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ወላይታ ድቻ በ43 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ተጋጣሚው ነገሌ አርሲ በ52 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።
ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አቻ የወጣው ወላይታ ድቻ የማሸነፍ መንገድን ለማግኘት ወደ ሜዳ ይገባል።
ካለፉት ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያገኘው ነገሌ አርሲ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ እና በዋንጫ ፉክክሩ ለመቆየት ሶስት ነጥብ ማግኘት ይኖርበታል።
ነገሌ አርሲ ካሸነፈ የሁለተኝነት ደረጃን ከመቻል የሚረከብ ሲሆን ከሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሶስት ዝቅ ያደርጋል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ከቀኑ ሰባት ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ42 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ46 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የ2016 ዓ.ም የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ33ኛ ሳምንት ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል።
ተጋጣሚው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ሶስት ነጥብ አላገኘም። ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታሉ።
ፋሲል ከነማ ከሸገር ከተማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በ33ኛ ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና የ2 ለ 1 ሽንፈት ያስተናገደው ፋሲል ከነማ በ46 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሸገር ከተማ በ40 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቡድኑ ባለፉት ሁለት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዷል።
ጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነታቸው ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።
ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ምድረ ገነት ሽሬ ከሀዲያ ሆሳዕና በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ምድረ ገነት ሽሬ በ37 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ሀዲያ ሆሳዕና በ42 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በ33ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ምድረ ገነት ሽሬ ከነገሌ አርሲ፣ ሀዲያ ሆሳዕና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በተመሳሳይ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።
ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይፋለማሉ።
በተለይም ምድረ ገነት ሽሬ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት ሶስት ነጥብ ማግኘት ግድ ይለዋል።