ቀጥታ፡

ሀዋሳ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ድል ቀንቷቸዋል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 20/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵ ፕሪሚየር ሊግ የ34ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ሃዋሳ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን 1 ለ 0 አሸንፏል።


በረከት ሳሙኤል በ61ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል በፍጹም ቅጣት ምት አስቆጥሯል።

የሃዋሳ ከተማው የአማካይ ተጫዋች ያሬድ ብሩክ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።

ከ10 ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ሃዋሳ ከተማ በ48 ነጥብ ደረጃውን ከሰባተኛ ወደ አራተኛ ከፍ አድርጓል። በሊጉም 12ኛ ድሉን አስመዝግቧል።

በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ 12ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ቡና በ46 ነጥብ ከነበረበት አምስተኛ ደረጃ ወደ ስድስተኛ ዝቅ ብሏል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ሌላኛው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሬዳዋ ከተማን 2 ለ 1 ረቷል።

ብሩክ አለማየሁ እና ሀብታሙ ጉልላት የማሸነፊያ ጎሎቹን ከመረብ ጋር አገናኝተዋል።

አስራት ቱንጆ የድሬዳዋ ከተማን ብቸኛ ግብ አስቆጥሯል።

በሊጉ 12ኛ ድሉን ያስመዘገበው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ46 ነጥብ ከነበረበት 10ኛ ደረጃ ወደ 7ኛ ከፍ አድርጓል።

በአንጻሩ በውድድር 13ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ድሬዳዋ ከተማ በ35 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ድሬዳዋ ከተማ ባለፉት ስምንት የሊግ ጨዋታዎች ከድል ርቋል።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ መቻል ከአርባምንጭ ከተማ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም