በጂማ ከተማ የሥራ ዕድል የተመቻቸላቸው ወጣቶች ተጠቃሚነታቸው አድጓል - ኢዜአ አማርኛ
በጂማ ከተማ የሥራ ዕድል የተመቻቸላቸው ወጣቶች ተጠቃሚነታቸው አድጓል
ጂማ፣ ግንቦት 20/2018 (ኢዜአ)፦ በጂማ ከተማ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ወጣቶች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ገለጹ።
በከተማዋ የወጣቶችን የሥራ ዕድል ለማስፋት የግብርና፣ የቴክኖሎጂና የንግድ ሥልጠናዎችን በመስጠት፣ የመሥሪያና መሸጫ ቦታዎችን በማቅረብ እንዲሁም የገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ።
በከተማዋ ኢዜአ ያነጋገረው ወጣት አብዱረሂም ናስር እንደገለጸው፤ የከተማ አስተዳደሩ ባመቻቸለት የሥራ ዕድል በመጠቀም የዳቦ መጋገሪያ ማሽኖችን በጥራት አምርቶ ለገበያ እያቀረበ ይገኛል።
እነዚህ ማሽኖች ከውጭ የሚገቡ የዳቦ መጋገሪያ ምርቶችን በመተካት የውጭ ምንዛሬን ከማዳናቸው ባለፈ፣ ኃይል ቆጣቢ በመሆናቸው በገበያ ላይ ተመራጭ መሆናቸውን አስረድቷል።
ይህም ገቢውን ከመጨመር ባለፈ ለሌሎች ወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጥር እንዳገዘው ጠቁሟል።
በተመሳሳይ ዘመናዊ ቦርሳዎችንና የቆዳ ውጤቶችን በማምረት ለገበያ እያቀረቡ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል ደርሶልኝ ሽመልስ እና ሀብታሙ ጋዲሳ ይጠቀሳሉ።
ወጣቶቹ እንደሚያስረዱት፤ የሚያመርቷቸው የቆዳ ውጤቶች በቅርጽም ሆነ በጥራት የሸማቹን ፍላጎት ያሟሉ በመሆናቸው በገበያ ላይ ተወዳዳሪ መሆን ችለዋል።
ሥራቸውን ይበልጥ ለማስፋፋትም የከተማ አስተዳደሩ የብድርና የመሥሪያ ቦታ እንዳመቻቸላቸው ገልጸዋል።
የጂማ ከተማ የሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ አብዱልሀሚድ ኑረዲን በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በከተማዋ ለወጣቶች የሥራ ዕድልን ለማስፋፋት በርካታ የመሥሪያና የመሸጫ ሼዶች ተገንብተዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ ከ3 ሺህ በላይ በማኅበራት ለታቀፉ 20 ሺህ 160 ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ፣ ዕቅዱን በማሳለጥ 28 ሺህ 500 ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
የወጣቶቹን ስኬት ይበልጥ ለማገዝ የሥልጠናና የብድር አቅርቦት መመቻቸቱን የገለጹት ኃላፊው፤ በበጀት ዓመቱ እስካሁን 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የብድር አገልግሎት መቅረቡን ጠቁመዋል።
ለወጣቶቹ የሥራ ዕድልን ለማስፋፋትም ለቡና መፈልፈያ፣ ለዳቦና እንጀራ መጋገሪያ፣ ለቆዳና እንጨት ሥራዎች እንዲሁም ለሌሎችም ተኪ ምርቶች ማምረቻ የሚሆኑ ሼዶች መሰጠታቸውን አክለዋል።
ወደ ሥራ የገቡት ወጣቶች ምርቶቻቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕብረተሰቡ ከማቅረብ ባለፈ፣ ተኪ ምርቶችን በማምረት የሀገርን የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻላቸውንም አቶ አብዱልሀሚድ ገልጸዋል።