ቀጥታ፡

ለምክክር ሂደቱ ውጤታማነት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 20/2018(ኢዜአ)፦ ለሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ውጤታማነት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እያበረከቱ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በዋናው ሀገራዊ ጉባኤ ላይ የሚቀርቡ ረቂቅ አጀንዳዎች ለተባባሪ ባለድርሻ አካላት ቀርበው ግብዓት የማሰባሰብያ ውይይት እያካሄደ ይገኛል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በዚሁ ጊዜ፤ ኮሚሽኑ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ በስኬት መከናወኑን ገልፀው፤ ለምክክር ሂደቱ ውጤታማነት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

በምክክር ሂደቱ እንዲሳተፉ የተወከሉ በአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ ታላላቅ ህዝባዊ መድረኮች ላይ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ጠቁመው በዚህም በሁሉም ክልሎች፣ በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል።

የተቋማት እና ማህበራት፣ የወረዳ ማህበረሰብ ተወካዮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የዳያስፖራ፣ የመንግስት ተቋማት እና በሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ከታቀደው አንጻር የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ በስኬት ተከናውኗል ብለዋል።

ይህም በቀጣይ ለሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ መሰረት መጣሉን ጨምረው ተናግረዋል።

በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት የአጀንዳ ቀረጻ ስራው በማጠቃለያ ምዕራፍ ላይ ይገኛል ሲሉም ዋና ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ ብሄራዊ መግባባትን ለመፍጠር ግዙፍ ተልዕኮ ተጥሎበት እየሰራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋናውን ሀገራዊ ጉባኤ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ኮሚሽኑ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎችና የህብረተሰብ ክፍሎች ሲያከናውናቸው የቆዩትን የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቶች በይፋ አጠቃሎ፣ አሁን ላይ የተለዩትን ዋና ዋና የሀገራዊ ጉባኤ አጀንዳዎች ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ማቅረብና ተጨማሪ ግብዓቶችን የመሰብሰብ ስራ ላይ መሆኑንም ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ ባለው በዚህ አዲስ ምዕራፍ፣ ኮሚሽኑ ያዘጋጃቸውንና ያደራጃቸውን የአጀንዳ ረቂቆች ለተባባሪ ባለድርሻ አካላት እያቀረበ ይገኛል ሲሉ ጠቁመዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ይህንን የግብዓት ማሰባሰብ ሂደት ካጠናቀቀ በኋላ፣ የተገኙትን አዳዲስ ሀሳቦች በማካተት ለመጨረሻውና ዋናው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ አጀንዳ ይቀርባሉ ብለዋል።

ይህ የተደራጀ አጀንዳ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ተወካዮች በሚሳተፉበትና ታሪካዊው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ ቀርቦ ምክክር እንደሚደረግበትም ጠቁመዋል።

ኮሚሽኑ በቀጣይ ሀገራዊ ጉባኤውን ለመጥራት የምክክር አጀንዳዎችን መቅረጽና ተደራሽ ማድረግ የመሰሉ ስራዎች እንደሚከናወኑ አስታውቀዋል።

በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ከአራት ሺህ በላይ ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ ምክክር የሚያደርጉ በመሆኑ ለዚህም ስኬት የሁሉም ድጋፍ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም