ቀጥታ፡

በዲጂታል ክህሎት ራሳችንን እያበቃን ነው - ተማሪዎች

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 20/2018(ኢዜአ)፦ በአምስት ሚሊየን የኢትዮ-ኮደርስ መርሃ ግብር በመታገዝ በዲጂታል ክህሎት ራሳቸውን እያበቁ መሆናቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ገለጹ።

የአምስት ሚሊየን ኢትዮ ኮደርስ መርሃ ግብር በዲጂታል ሳይንስ ዘርፎች እንደ አንድሮይድ ማበልጸግ፣ ዳታ አናሊቲክስ፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና የዌብ ዲዛይን መሰረታዊ ስልጠናዎችን ያካተተ ነው። 

የመርሃ ግብሩ ዋነኛ ዓላማና ግብ አምስት ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን በዲጂታል ክህሎት በማብቃት፣ ሀገሪቱ በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ያላትን ተወዳዳሪነት ማረጋገጥ ነው።

ይህም ለወጣቶች ዓለምአቀፋዊ ዕውቅና ያለው ሰርቲፊኬት እና የስራ ዕድሎችን በመፍጠር በኩል ዓይነተኛ ሚና  እየተጫወተ ይገኛል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎቹ እንደገለጹት ከመደበኛው ትምህርት በተጨማሪ ራሳቸውን ከዲጂታሉ ዓለም ጋር ለማላመድ ጥረት እያደረጉ ነው።

በለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው አቢጊያ ዳንኤል፣ ወደፊት የሶፍትዌር ኢንጂነር የመሆን ህልሟን ለማሳካት በትምህርት ቤትና በሀገር አቀፍ ደረጃ የተመቻቹ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕድሎችን እየተጠቀመች መሆኗን ገልጻለች።

በዚሁ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው አላዛር ማስሬ፣ በዲጂታል ዘርፍ ራሱን እያበቃ መሆኑን ገልጾ፤ ትውልዱ ነገ ተወዳዳሪ ዜጋ ለመሆን ራሱን ከቴክኖሎጂ ጋር ማላመድ የግድ መሆኑን ተናግሯል።

በድልበር አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው አቤል ሙሉጌታ በበኩሉ፣ የአምስት ሚሊየን ኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና መውሰዱን ገልጾ፣ ተማሪዎች ከቴክኖሎጂ ጋር ለመራመድ የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ እንዲጠቀሙበት መክሯል።

የዌብ ዲዛይን ስልጠና መውሰዱንና ይህም በዘርፉ ያለውን መሰረታዊ እውቀት እንዳስጨበጠው የተናገረው ደግሞ ተማሪ  ፍራኦል ተሾመ ነው።


 

የለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሰለሞን ዲሮ ትምህርት ቤቱ ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስና በሌሎች የቴክኖሎጂ ዘርፎች ለተማሪዎች ስልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

የድልበር አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር ተመስገን ቶሊና በበኩላቸው፣ ተማሪዎችና መምህራን የ5 ሚሊየን ኢትዮ ኮደርስ ስልጠና እንዲወስዱ ትምህርት ቤቱ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም