የኮሌራና የወባ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኮሌራና የወባ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው
ባህር ዳር፤ ግንቦት 20/2018(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በክረምት መግቢያና መውጫ ወቅት የሚከሰቱ የኮሌራና የወባ በሽታዎችን መከላከል የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ኢንስቲትዩቱ የሚከሰቱ በሽታዎችን ቀድሞ በመከላከል ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል።
የሚስተዋሉ የጤና ስጋቶችን ቀድሞ በመተንበይ፣ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ፣ አስፈላጊውን የሰው ኃይል፣ የሕክምና ግብዓትና በጀት በመመደብ የመከላከል ስራውን ለማቀላጠፍ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የክረምቱን መግባት ተከትሎ እስከ ታኅሣሥ 30 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ የሚዘልቅ የወባና የኮሌራ በሽታዎች የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።
ያለፉ ዓመታት መረጃዎች የሚያሳዩት በክረምት መግቢያና መውጫ ወቅት በዝናብ ስርጭት መቆራረጥ ሳቢያ በየቦታው የሚታቆረው ውሃ ለኮሌራና ወባ በሽታዎች ስርጭት መስፋፋት መንስኤ መሆኑን ጠቁመዋል።
ችግሩን ለመቅረፍም ሃብትን፣ የሰው ሃይልንና እውቀትን በማስተባበር የህብረተሰቡን ጤና በመጠበቅ በማምረት ስራው ላይ እንዲያተኩር የማድረግ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
የኮሌራ በሽታን ለመከላከል ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር የእቅዱ አካል ነው ብለዋል።
የወባ ወረርሽኝን ለመግታት ባለፈው ዓመት የተጀመረውን "የአርብ ቀን እጆች" ንቅናቄን አጠናክሮ በማስቀጠል በየሳምንቱ ህዝቡ በነቂስ በመውጣት ውሃ ያቆረ ቦታን በማፋሰስ ሌሎች የአካባቢ ቁጥጥር ተግባራትን ያከናውናል ነው ያሉት።
እቅዱን ለማሳካትም በዞንና በወረዳ ከሚገኙ የጤና መዋቅሮችና የአደጋ ማስተባበሪያ ማዕከላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም ጠቅሰዋል።