ቀጥታ፡

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የምርምር ቴክኖሎጂዎችን እያጎለበተ ነው

ሐረማያ፤ ግንቦት 20/2018 (ኢዜአ)፦ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የምርምር ቴክኖሎጂዎችን እያጎለበተ እንደሚገኝ አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው 43ኛውን ዓመታዊ የምርምርና የማህበረሰብ ተሳትፎ ግምገማ ጉባዔ ’’ለአካባቢ ተስማሚ ፈጠራና ስነ ምህዳር ጥበቃ ለጽኑ ማህበረሰብ ግንባታ’’ በሚል መሪ ሀሳብ እያካሄደ ነው።

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ ጉድኝት ምክትል ፕሬዝዳንት ይስሃቅ ዩስፍ(ዶ/ር) በወቅቱ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው በግብርና፣ በጤና፣ በቴክኖሎጂ፣ በትምህርት፣ በህግ፣ በህብረተሰብ ሳይንስና በሌሎችም የምርምር ተግባራት እያከናወነ ነው።


 

በተለይም ዘንድሮ ዩኒቨርሲቲው 116 ፕሮጀክቶች ላይ የምርምር ስራ እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ ከዚህ ውስጥም 42ቱ መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከ1 ቢሊየን ብር በላይ በጀት በመመደብ የሚያከናውናቸው የጥናትና ምርምር ቴክኖሎጂዎችም የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጡ እንደሚገኙም አስታውቀዋል።

ዩኒቨርሲቲው በዘንድሮ ዓመትም ከ95 በላይ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ማሰራጨቱን አመልክተዋል።

በዩኒቨርሲቲው ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና አስተዳደር ጋር በተያያዘ በድሬዳዋ አስተዳደር፣ በሐረማያ ሀይቅ፣ በአዴሌ፣ ደንጋጎ እና ሌሎች ተፋሰስ አካባቢዎች ላይ የተቀናጀ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በማህበረሰብ አገልግሎትና ተሳትፎ በኩልም ከ150ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ነፃ የህግ አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ በጤና፣ በትምህርትና በሌሎች ዘርፎች አመርቂ ተግባራት ማከናወኑን አንስተዋል።

የግምገማ መድረኩ ዩኒቨርሲቲው የሚያከናውናቸውን አበረታች ስራዎች ለማስቀጠልና የሚስተዋሉ ውስንነቶች ለመቅረፍ እንደሚያስችል ተመላክቷል።

ዩኒቨርሲቲው ለ43ኛ ጊዜ በሚያካሂደው የምርምርና የማህበረሰብ ተሳትፎ ጉባዔ 32 የምርምር ውጤቶች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሏል።

ለሶስት ቀናት በተሰናዳው በዚሁ ጉባዔ ላይ የዩኒቨርሲቲው ምሁራንና ተመራማሪዎች፣ ሴክተር መስሪያ ቤቶች፣ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የማህበረሰብ ተወካዮች፣ አባ ገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም