ቀጥታ፡

በአማራ ክልል በዘንድሮው መኸር እርሻ ከ876 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በሰሊጥና አኩሪ አተር ይለማል

ባህርዳር ፤ ግንቦት 20/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በዘንድሮው መኸር እርሻ ከ876ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ለኢንዱስትሪና ለውጭ ገበያ የሚውል የሰሊጥና የአኩሪ አተር እንደሚለማ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

ሰሊጥ ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገኙ የግብርና ምርቶች መካከል ተጠቃሽ ነው።

አኩሪ አተርም ለምግብ ዘይት ፋብሪካዎችና ለእንስሳት መኖ ኢንዱስትሪዎች ወሳኝ ግብዓት ከመሆኑም በላይ፣ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ያለው ተፈላጊነት እየጨመረ የመጣ ሰብል ነው።

‎በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለፁት ለኢንዱስትሪና ለወጪ ምርት ግብዓት የሚውሉ ሰብሎችን በጥራትና በብዛት ለማምረት ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው።




‎በዚህም በዘንድሮው የመኸር እርሻ የአየር ንበረታቸውና ስነ ምህዳራቸው ተስማሚ በሆኑ አካባቢዎች የሰሊጥና አኩሪ አተር ሰብሎች በስፋት ለማልማት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።

በዚህም በክልሉ ከሚለማው 876ሺህ 870 ሄክታር መሬት፤ 463ሺህ 566 ሄክታር በሰሊጥ ቀሪው ደግሞ በአኩሪ አተር እንደሚለማ ተናግረዋል።

‌‎ከልማቱ ከ15 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ጠቁመው የዘር ወቅት በመድረሱም ዘርና ማዳበሪያ እየቀረበ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም