መቻል ከሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
መቻል ከሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 20/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከኢትዮጵያ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ መርሐ ግብር በኋላ ዛሬ በ34ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ወደ ውድድር ይመለሳል።
ከመርሐ ግብሮቹ መካከል ምሽት 12 ሰዓት ላይ መቻል እና አርባምንጭ ከተማን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታ ተጠቃሽ ነው።
መቻል በ53 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። አርባምንጭ ከተማ በ29 ነጥብ የመጨረሻው 20ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በ33ኛ ሳምንት ከባህር ዳር ከተማ ጋር አንድ አቻ የተለያየው መቻል ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ ይጫወታል።
መቻል ድል ከቀናት ከሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ዝቅ ያደርጋል።
ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ከድል የራቀው አርባምንጭ ከተማ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት ያለውን ተስፋ ለማለምለም የግድ ሶስት ነጥብ ማግኘት ይጠበቅበታል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ድሬዳዋ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ድሬዳዋ ከተማ በ35 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ43 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ባለፉት ሰባት የሊግ ጨዋታዎች ከድል የራቀው ድሬዳዋ ከተማ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት በሚያደርገው ትግል ሶስት ነጥብ ያስፈልገዋል።
በ33ኛ ሳምንት ሃዋሳ ከተማን 1 ለ 0 ያሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ በድል ጉዞው ለመቀጠል ይጫወታል።
ሃዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
ባለፉት 10 የሊግ ጨዋታዎች ከድል የራቀው ሃዋሳ ከተማ በ45 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል። ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና በ46 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በ33ኛ ሳምንት ፋሲል ከነማን 2 ለ 1 በማሸነፍ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ኢትዮጵያ ቡና ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 34ኛ ሳምንት መርሐ ግብር እስከ ግንቦት 22 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
ሲዳማ ቡና በ58 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።
የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን አቤል ያለው ከሲዳማ ቡና በ14 ጎሎች እየመራ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮቹ ናትናኤል ዳንኤል እና አዲስ ግደይ፣ የፋሲል ከነማው ታምራት ኢያሱ በተመሳሳይ 11 ግቦች ይከተላሉ።