ክሪስታል ፓላስ የአውሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ ዋንጫን አነሳ - ኢዜአ አማርኛ
ክሪስታል ፓላስ የአውሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ ዋንጫን አነሳ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 19/2018 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ኮንፍረንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ክሪስታል ፓላስ ራዮ ቫዮካኖን 1 ለ 0 አሸንፏል።
ማምሻውን በጀርመን ላይፕዚግ ሬድ ቡል አሬና ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ጂን-ፍሊፕ ማቴታ በ51ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል።
የለንደኑ ክለብ ፓላስ በሁለተኛው አጋማሽ ባሳየው የተሻለ እንቅስቃሴ እና በፈጠራቸው የግብ እድሎች አሸናፊ ሆኗል።
የማድሪዱ ክለብ ራዮ ቫዮካኖ ግልጽ የግብ እድሎችን መፍጠር አልቻለም።
ውጤቱን ተከትሎ ክሪስታል ፓላስ የኮንፍረንስ ሊግ አሸናፊ ሆኗል።
ፓላስ በአውሮፓ መድረክ ዋንጫ ሲያነሳ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን
የለንደኑ ክለብ የአውሮፓ መድረክ ዋንጫን ለማንሳት 175 ዓመታትን ጠብቋል።
የ51 ዓመቱ የክሪስታል ፓላስ አሰልጣኝ ኦሊቨር ግላስነር ለቡድኑ ዋንጫውን በማስገኘት ታሪክ ሰርተዋል።
ግላስነር ባለፈው ዓመት ቡድኑን ለኤፍኤ ካፕ ክብር ማብቃታቸው የሚታወስ ነው።
አሰልጣኙ በመጨረሻ ጨዋታቸው ፓላስን የዋንጫ አሸናፊ አድርገውታል።
ክሪስታል ፓላስ የውድድሩ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ በቀጣይ ዓመት ለሚካሄደው የዩሮፓ ሊግ ውድድር ምድብ ድልድል በቀጥታ ማለፉን አረጋግጧል።
የፓላስን ድል ተከትሎ በቀጣዩ ዓመት በተለያዩ የአውሮፓ መድረኮች የሚጫወቱ የእንግሊዝ ክለቦች ብዛት ዘጠኝ ደርሷል።
በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ለትልቅ ፍጻሜ የበቃው ራዮ ቫዮካኖ የዋንጫ ህልሙ ሳይሳካ ቀርቷል።
የኢንጎ ፔሬዙ ቫዮካኖ ለውድድሩ ፍጻሜ በመድረሱ እና ባሳየው ትግል ከብዙዎች አድናቆቶ ተችሮታል።