ቀጥታ፡

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያ አሸናፊነት የሚበሰርበት ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 19/2018(ኢዜአ)፦ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሕዝብ ድምፅ የኢትዮጵያ አሸናፊነት የሚበሰርበት መሆኑን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ ገለጹ።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም መራጮች ድምፅ ይሰጣሉ።

ድምፅ ከሚሰጥበት የጠቅላላ ምርጫ ዕለት አስቀድሞ የሚቀጥሉት አራት ቀናት የጥሞና ወቅት ሲሆኑ፤ በአካልና በአደባባይ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችንና የመገናኛ ብዙኅን አጠቃቀምን ይገድባሉ።

በዚህም በአካልና በአደባባይ የፖለቲካ ተኮር የህዝብ ስብሰባዎችና ሰልፎች፣ የቤት ለቤትና የአደባባይ እንቅስቃሴዎች፣ የቅስቀሳ ኅትመቶችንና ቁሳቁሶችን መለጠፍ እንዲሁም የቅስቀሳ አልባሳትን መልበስ በጥበቅ የተከለከሉ ተግባራት ናቸው።

በመገናኛ ብዙኅን በቀጥታም ሆነ በተቀረጹ የዕጩዎች ወይም የፓርቲ ፕሮግራሞች ሥርጭት፣ የማኅበራዊ ትሥሥር ገጾችን በመጠቀም ቅስቀሳ ማድረግ፣ ፕሮጀክት ማስጀመርና ማስመረቅ እንዲሁም በምርጫ ቦርድ መመሪያዎች ላይ ያልተደነገጉ ምርጫ ተኮር ተግባራትን መፈፀም በጥብቅ ተከልክሏል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሰሞኑ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫም ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ ሁሉም የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ምክር ቤቱ የስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ልምድና ተሞክሮ በመቀመር ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት እየሰራ ነው።

የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ቅድመ ዝግጅትና የዲጂታል ዕጩዎች ምዝገባ ሂደት በስኬት ምዕራፍ ማጠናቀቅ እንደተቻለ ገልጸዋል።

በዚህም የምክር ቤቱ አባል የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃ የአየር ሰዓት የፖሊሲ አማራጭ ማቀረባቸውን አመልክተው፤ በተለያዩ አካላት በተዘጋጁ የክርክር መድረኮች የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በፍትሐዊነት ለህዝብ ሃሳባቸውን ማስተዋወቅ መቻላቸውንም ተናግረዋል።

የምርጫ ተከታታይ ኮሚቴ በማቋቋም ከምርጫ ቦርድ ጋር በመሆን ለጠቅላላ ምርጫ ሂደቱ አስቻይ ሁኔታዎችን ለማጥናትና ለመለየት ትልቅ ዕድል መፍጠሩንም አንስተዋል።

ይህ የምርጫ ጉዳዮችን የሚከታተል ዴስክ አጠቃላይ ሁኔታዎችን በመገምገም፣ ስኬታማ ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መኖሩን በቅርበት መከታተሉን አስታውቀዋል።

ከግንቦት 20 ጀምሮ የጥሞና ጊዜ በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ ሕጉ ተገዢ በመሆን ለዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት በአርዓያነት እንዲሰሩም አሳስበዋል።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫው ኢትዮጵያ የምታሸንፍበት መሆኑንም ጨምረው አብራርተዋል።

ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ላይ መራጩ ሕዝብ እንደተለመደው ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር እንዲያረጋግጥ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም