ባሕር ዳር ለነዋሪዎቿ ምቹ ለዓለምአቀፍ ጎብኚዎች ደግሞ ተመራጭ የቱሪስት ከተማ እየሆነች ነው - ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው - ኢዜአ አማርኛ
ባሕር ዳር ለነዋሪዎቿ ምቹ ለዓለምአቀፍ ጎብኚዎች ደግሞ ተመራጭ የቱሪስት ከተማ እየሆነች ነው - ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 19/2018(ኢዜአ)፦ ባሕር ዳር በኮሪደር ልማት ለነዋሪዎቿ ምቹ ለዓለምአቀፍ ጎብኚዎች ደግሞ ተመራጭ የቱሪስት ከተማ እየሆነች ነው ሲሉ የባህርዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ገለጹ።
የባሕር ዳር ከተማን ውበትና ፅዳት በመጠበቅ ለነዋሪዎች ምቹ፣ ለዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ደግሞ ተመራጭና ረጅም ጊዜ የሚቆዩባት የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የተቀረጸው ዕቅድ በተግባር እየተተረጎመ ይገኛል።
የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው እንደገለጹት፣ ይህንን ግብ ለማሳካት የተቋቋመው የስማርት ባህርዳር ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት መሪነቱን በመውሰድ የኮሪደርና የጣና ዳርቻ ልማቶችን ሌሊትና ቀን በከፍተኛ ፍጥነት እያከናወነ ነው።
የከተማዋን ገጽታ የቀየሩ የጣና እና የዓባይ ዳርቻ ፕሮጀክቶች
የከተማዋ ተፈጥሯዊ ሀብቶች የሆኑትን የጣና ሐይቅንና የዓባይ ወንዝን ለቱሪዝም ምቹ የማድረግ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶታል ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅት በሐይቁ ዳርቻ ላይ ዘጠኝ የሚደርሱ ቦታዎች መልማታቸውን ጨምረው አስታውቀዋል።
ይህም ከተማዋ፣ ነዋሪዎችና ጎብኚዎች ከሐይቁ ጋር ያላቸውን መስተጋብር በእጅጉ አሳድጎታል ብለዋል።
ከዚሁ ልማት ጋር ተያይዞም የዘንባባ ፓርክ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ የከተማዋን ውበት ይበልጥ እንዳደመቀው ገልጸዋል።
የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ዋና ዋና መስመሮች እያደሰ ያለው የኮሪደር ልማት ከደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ እስከ ዓባይ ማዶ ባለው ዋና መንገድ ላይ በከፍተኛ ፍጥነት እየተገነባ ይገኛል ብለዋል።
ይህ መሠረተ ልማት ከ5 እስከ 7 ሜትር የሚደርስ ሰፊ የእግረኛ መንገድ፣ እስከ 4 ሜትር ስፋት ያላቸው ውብ አረንጓዴ መናፈሻዎች፣ እስከ 3 ሜትር ስፋት ያለው የተለየ የብስክሌት መንገድ፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ የሕዝብ ማረፊያዎችና የሕፃናት መጫወቻዎች ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን እስከ ፓፒረስ ሆቴል ድረስ ያለው የእግረኛ መንገድ ግንባታ እየተፋጠነ እንደሚገኝም አንስተዋል።
በከተማዋ የዓባይ ወንዝን ዳርቻን ለማልማት መታቀዱንም ነው የጠቆሙት።
የከተማዋ የኮሪደር ልማት ዕቅድ ሲቀረጽ ጀምሮ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የፌደራል መንግሥቱ ፕሮጀክቱን በመገምገምና አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ የላቀ የመሪነት ሚና መጫወታቸውንም አስረድተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በከተማዋ ተገኝተው የልማት ሥራዎቹን መገምገማቸውንና ለቀጣይ ተግባራት አቅጣጫ ማስቀመጣቸውንም ነው ያነሱት አቶ ጎሹ እንዳላማው።
ለኮሪደር ልማቱ ስኬት የከተማዋ ነዋሪዎችና ባለሀብቶች በገንዘብና በሐሳብ እያደረጉት ያለው ተሳትፎ አይተኬ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሰል የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አረጋግጠዋል።