ቀጥታ፡

በጠቅላላ ምርጫው ሀገራችንን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግር የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል - የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች

ነቀምቴ፤ ግንቦት 19/2018(ኢዜአ)፦ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሀገርን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግር የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ነዋሪዎቹ በምርጫው ለሀገር የሚበጅ፣ የተጀመሩ የልማትና የእድገት ጉዞዎችን የሚያስቀጥል እንዲሁም የሀገሪቱን አንድነት የሚያስጠብቅ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ነው የገለጹት።


 

የነቀምቴ ከተማ ነዋሪው መንገሻ አከዩ፤ በሚዲያ ተቋማት በሚተላለፉ የፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳዎች አማካኝነት በቂ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ምርጫ በመንግሥትና በህብረተሰቡ መካከል መግባባትን ከሚፈጥሩ ዋና ዋና ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ህብረተሰቡ ይበጀኛል ያለውን አካል እንዲመርጥ እድል የሚሰጥ በመሆኑ ለሀገር ሰላም፣ አንድነትና እኩልነት የሚሰራን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።


 

ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ መስታወት ብርሃኑ በበኩላቸው፤ በመጪው ሀገራዊ ምርጫ በነፃነት ያመኑበትን ፓርቲ ለመምረጥና ድምፃቸውን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

ከተለያዩ አካላት በተሰጡ የግንዛቤ ማስጨበጫዎች የፓርቲዎችን ምልክት ለይተው ማወቅ መቻላቸውንና ካርድ መውሰዳቸውን ገልጸው፣ ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም አክለው ተናግረዋል።


 

በተመሳሳይ ሌላኛው ነዋሪ ምስጋኑ ጣሶ፤ በምርጫው ወቅት የሚጠበቅባቸውን የዜግነት ግዴታ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸው፣ ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እና ልማት ይበጃል ያሉትን ፓርቲ እንደሚመርጡ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም