ቀጥታ፡

በምርጫ ክርክሩና በቅስቀሳው የፖሊሲና የስትራቴጂ አማራጮቻችንን ለህዝቡ በሚገባ አቅርበናል - የፖለቲካ ፓርቲዎች

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 19/2018 (ኢዜአ) የምርጫ ክርክሩና የቅስቀሳ መድረኮቹ የፖሊሲና የስትራቴጂ አማራጮቻቸውን ለህዝቡ በሚገባ ለማስተዋወቅ ሰፊ ዕድል እንደፈጠሩላቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በመጪው ግንቦት 24 ቀን 2018 . እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያስታወቀ ሲሆን፣ 50 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን አመልክቷል።

ከግንቦት 20 እስከ ግንቦት 23 ቀን 2018 . ድረስ ማንኛውም ዓይነት የምርጫ ቅስቀሳ የማይደረግበት የጥሞና ጊዜ ነው።

የተወዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችም የፖሊሲ አማራጮቻቸውንና ማኒፌስቶዎቻቸውን ለህዝብ ሲያስተዋውቁና የምርጫ ክርክሮችን ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወቃል።

ይህንን ሂደት አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ በምርጫ ክርክሩና በቅስቀሳ መድረኮች ላይ የየራሳቸውን የፖሊሲና የስትራቴጂ አማራጮች ለህዝቡ በሚገባ ማቅረብ መቻላቸውን ገልጸዋል።




የህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር እና የምርጫ ዴስክ አስተባባሪ አበራ በቀለ፤ ፓርቲያቸው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ዓላማ መግለጫ (ማኒፌስቶ) በማዘጋጀት ለህብረተሰቡ አቅርቦ ቅስቀሳ ማድረጉን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት ፓርቲው ያዘጋጃቸውን የተለያዩ የፖሊሲ አማራጮች እና የስትራቴጂ ማስፈጸሚያ ስልቶች ለህዝቡ በስፋት ማስተዋወቁን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የሰዓት ድልድል መሠረት፣ መገናኛ ብዙሃን የፖለቲካ ፓርቲዎች በክርክሮች ላይ የየራሳቸውን ሐሳብ እንዲያንሸራሽሩ በማመቻቸት በኩል ገንቢ ሚና መጫወታቸውንም አብራርተዋል።

አሁን የተደረገውን የምርጫ ቅስቀሳ እና የተሰጠውን የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ጋር ሲነጻጸር እጅግ የተሻለ መሆኑን ገልጸዋል።

ፓርቲው በዕጩነት በሚወዳደርባቸው ዘጠኝ ክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮች ውስጥ የምርጫ ቅስቀሳዎችን በተከታታይ ሲያከናውን መቆየቱንም አስታውቀዋል።

የፓርቲው አመራሮችና አባላት ቤት ለቤት በመዘዋወርና በራሪ ወረቀቶችን በማሰራጨት ባደረጉት የቅስቀሳ ሥራ ማከናወናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ሀገርን ማቀጠል የሚችል ጠንካራ እና ህጋዊ መንግስት መመስረት የሚችለው በምርጫና በምርጫ ብቻ መሆኑን ተገንዝቦ፣ ሂደቱ እንዲሳካ የበኩሉን አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበትም ገልጸዋል።

ህዝቡ የእያንዳንዱን የምርጫ ካርድ ዋጋና ክብደት በሚገባ በመረዳት፣ በምርጫው ዕለት ይበጀኛል የሚለውን ፓርቲ እንዲመርጥም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ከምርጫ ውጪ ሌላ የፖለቲካ ሥልጣን ሽግግር መንገድ ሊኖር እንደማይገባ የገለጹት አቶ አበራ፤ በሐሳብ የበላይነት ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ልምምድ እንዲዳብር የህዝቡ ተሳትፎ ወሳኝ ድርሻ እንዳለው አስገንዝበዋል።




የህዳሴ ፓርቲ ፕሬዝዳንት የማነ አሰፋ በበኩላቸው፤ ፓርቲያቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ጋር በመተባበር በመደበው የአየር ሰዓት በመጠቀም፣ የፖለቲካ ዓላማ መግለጫውን (ማኒፌስቶውን) እና አማራጭ ሐሳቦቹን በተለያዩ ሚዲያዎች ለህዝብ በሚገባ ማቅረቡን ገልጸዋል።

ፓርቲው ያዘጋጃቸውን የፖሊሲና የሐሳብ አማራጮች ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ የተሻለ ሥራ ማከናወኑንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በራሪ ወረቀቶችን በማደል፣ ቤት ለቤት በመዘዋወርና የተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾችን (ሶሻል ሚዲያ) እንደ አማራጭ በመጠቀም ማኒፌስቶውንና ፖሊሲውን ሲያስተዋውቅ መቆየቱን ተናግረዋል።

የህዳሴ ፓርቲ ከተለመደው የመወቃቀስ እና የብሽሽቅ ፖለቲካ አዙሪት ወጥቶ፣ በሐሳብ መሪነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ እሳቤና በውይይት የሚያምን የፖለቲካ ባህልን እየተከተለ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ፓርቲያቸው በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የምርጫ ቅስቀሳዎችን ባደረገበት ወቅት ምንም ዓይነት የጸጥታም ሆነ የሌላ ችግር እንዳልገጠመውም ሊቀ መንበሩ ገልጸዋል።

ለዚህም ሰላማዊ የቅስቀሳ ሂደት መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ ላደረጉት የጸጥታ አካላት እና የመንግስት መዋቅሮች ምስጋና አቅርበዋል።

በአጠቃላይ በምርጫ ክርክሩና በቅስቀሳው ወቅት ፓርቲዎች የየራሳቸውን ሐሳብ በነፃነት ማንሸራሸር መቻላቸው ለሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር መጎልበት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አንስተዋል።

በመጨረሻም ሊቀ መንበሩ ህዝቡ የተሰጠውን የምርጫ ካርድ በአግባቡ በመጠቀም ይበጀኛል፣ ያስተዳድረኛል የሚለውን ፓርቲ በነፃነት እንዲመርጥ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም