ህዝቡ ዴሞክራሲያዊ መብቱን በአግባቡ መጠቀም እንዲችል ከጸጥታ አንጻር በቂ ዝግጅት ተድርጓል - የአማራ ክልል ፖሊስ - ኢዜአ አማርኛ
ህዝቡ ዴሞክራሲያዊ መብቱን በአግባቡ መጠቀም እንዲችል ከጸጥታ አንጻር በቂ ዝግጅት ተድርጓል - የአማራ ክልል ፖሊስ
ባህር ዳር፤ ግንቦት 19/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ህዝቡ በጠቅላላ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ መብቱን በአግባቡ መጠቀም እንዲችል ከጸጥታ አንጻር በቂ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።
የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊነት የተደረጉ ዝግጅቶችን አስመልክተው ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ በክልሉ በተቀናጀ አግባብ በተሰራው የሰላም ማስከበር ስራ ውጤት ተመዝግቧል።
በተለይም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ የሚያስችሉ፣ ፀጥታን የሚያጠናክሩ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
የክልሉ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ መብቱን በአግባቡ መጠቀም እንዲችል ከጸጥታ አንጻር በቂ ዝግጅት መደረጉንም አረጋግጠዋል።
ህዝቡ ሰላምን የሚያጠናክር እንቅስቃሴን በቁርጠኝነት እያገዘና እየደገፈ እንደሆነም አስረድተዋል።
የክልሉ ፖሊስ ከህብረተሰቡና ከሌሎች የፀጥታ መዋቅሮች ጋር በመሆን ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።