ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በያቤሎ ከተማ የሚገኘውን የቦረና ባሕል ማዕከል መረቁ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 19 /2018 (ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በያቤሎ ከተማ የሚገኘውን የቦረና ባሕል ማዕከል ዛሬ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምረቃው ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በ2013 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ ተቀምጦለት የነበረውና ዛሬ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው የባህል ማዕከል፤ በመደመር መጽሐፍ ሽያጭ የተገነባ መሆኑን ጠቁመዋል።

የባሕል ማዕከሉ በ57.6 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ እንደሆነም ገልጸዋል።

ማዕከሉ የገዳን ሥርዓት ለማሳየት በልዩ ሁኔታ ዲዛይን የተደረገ ሲሆን በአንድ ጊዜ እስከ 2000 ሰዎች ማስተናገድ አቅም ያለው የስብሰባ አዳራሽ እና የቅርስ ሙዚየምን አካቶ መገንባቱን አመልክተዋል።

በተጨማሪም ማዕከሉ የቦረናን ህዝብ ባሕል፣ ታሪክ እና ፍልስፍና ለትውልድ የማሸጋገር ቁልፍ ሚና ይኖረዋልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም