የአዲስ አበባ ፖሊስን ተቋማዊ ጥንካሬና ክብር የሚያስጠብቅ ውጤታማ የሪፎርም እርምጃ እየተወሰደ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ፖሊስን ተቋማዊ ጥንካሬና ክብር የሚያስጠብቅ ውጤታማ የሪፎርም እርምጃ እየተወሰደ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 19/2018(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ፖሊስን ተቋማዊ ጥንካሬና ክብር የሚያስጠብቅ ውጤታማ የሪፎርም እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ በ100 ቀናት ዕቅድ የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች አፈፃጸም ማጠቃለያ የግምገማ መድረክ በዓድዋ ድል መታሰቢያ አካሂዷል።
በመድረኩ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ እንዲሁም የጠቅላይ መምሪያው ከፍተኛ አመራሮችና አባላት ተገኝተዋል።
ከንቲባ አዳነች በዚሁ ጊዜ፤ በሀገራዊ ለውጡ ማግስት በፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ተልዕኮን በብቃት መወጣት የሚያስችል ውጤታማ የሪፎርም እርምጃ መወሰዱን አስታውሰዋል።
በፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ከተወሰደው ውጤታማ የለውጥ እርምጃ አንፃርም የአዲስ አበባ ፖሊስ ተልዕኮን በብቃት መወጣት የሚያስችል ሪፎርም እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።
በዚህም የአዲስ አበባ ፖሊስን ተቋማዊ ጥንካሬና ክብር የሚያስጠብቅ ውጤታማ የሪፎርም እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አንስተዋል።
በተቋሙ የሪፎርም እርምጃ የሚደረገው ድጋፍና ክትትልም የሠራዊቱን ሎጀስቲክስ፣ ሞራልና ሙያዊ ሥነ-ምግባር በመገንባት ተልዕኮን በብቃት መወጣት የሚያስችል እንደሆነ አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ 3ኛዋን ዓለምአቀፍ የዲፕሎማሲ ማዕከል ከተማ ሰላምና ደኅንነትን በማስጠበቅ በወንጀል መከላከልና የሕግ የበላይነትን በማስፈን የተጣለበትን ከፍተኛ ኃላፊነት እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የፖሊስ ሠራዊትን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለመፍታት የመጀመሪያው ምዕራፍ የመኖሪያ መንደር ግንባታ በመጪው ሰኔ ወር እንደሚጀመር አስታውቀዋል።
በቀጣይም ፖሊስ በመዲናዋ ለሚከናወኑ ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎች የሚያበረክተውን ጉልህ አስተዋጽኦ የበለጠ በማላቅ ከከተማዋ ፈጣን ዕድገት ጋር አብሮ መጓዝ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል አስራት ዴኔሮ በበኩላቸው፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ 118 ዓመታትን ያስቆጠረ ታሪክ ያለው አንጋፋ ተቋም መሆኑን አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅትም የመዲናዋን ሰላምና ደኅንነት 24/7 በማስጠበቅ ግዳጁን በብቃት እየተወጣ መሆኑንም ተናግረዋል።
የተቋሙ ሁለንተናዊ የሪፎርም እርምጃ ተቋማዊ ተልዕኮን በብቃት በመወጣት የሠራዊት አባላቱን ጥቅምና ክብር የሚያስጠብቅ መሆኑን ገልጸዋል።