ለህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ይሰጣል ለምንለው ፓርቲ ደምጻችንን ለመስጠት ተዘጋጅተናል -የሃዋሳ ከተማና የዎንሾ ወረዳ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ይሰጣል ለምንለው ፓርቲ ደምጻችንን ለመስጠት ተዘጋጅተናል -የሃዋሳ ከተማና የዎንሾ ወረዳ ነዋሪዎች
ሃዋሳ፤ ግንቦት 19/2018 (ኢዜአ)፦ ለህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ይሰጣል ለሚሉት ፓርቲ ድምጻቸውን በመስጠት ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን በሲዳማ ክልል የሃዋሳ ከተማ እና የዎንሾ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
ነዋሪዎቹ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ በወቅቱ ወስደው የድምጽ መስጫውን ቀን እየተጠባበቁ መሆናቸውንም ለኢዜአ ተናግረዋል።
ግንቦት 24 ቀን በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ለህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል ለሚሉት ፓርቲ ድምጻቸውን በመስጠት ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን እንደሚጠቀሙም ገልጸዋል፡፡
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካካል የሃዋሳ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ጽጌ ይልማ የወሰዱትን ካርድ ተጠቅመው ለሀገርና ለሀዝብ የተሻለ አማራጭ ያለውን ፓርቲ ለመምረጥ እንደተዘጋጁ ተናግረዋል፡፡
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በቴክኖሎጂ ታግዞ የሚካሄድ መሆኑ ለየት ያደርገዋል ብለዋል።
ለምርጫው የሚሳተፉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያደረጉትን ቅስቀሳና የፖሊሲ አማራጭ በመገናኛ ብዙሀን መከታተላቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ አበራሽ ዋጄቦ ናቸው፡፡
በዚህም በድምጽ መስጫው ቀን ለህዝብ ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች ምላሽ ለሚሰጥ ፓርቲ ድምጻቸውን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
ዕድሜያቸው ለመራጭነት የደረሱ ልጆቻቸው ጭምር ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ መውሰዳቸውን የሚናገሩት ደግሞ የዎንሾ ወረዳ ነዋሪ አቶ ባቢሶ ባራሞ ናቸው።
በመጪው ሰኞ በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ለህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል ለሚሉት ፓርቲ ድምጻቸውን ለመስጠት እንደተዘጋጁ ተናግረው፣ ዜጎች ካርዳቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙበት እየቀሰቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሌላው የዚሁ ወረዳ ነዋሪ መምህር ብርሃኑ ቢሊሶ በበኩላቸው የምርጫ ካርድ በወቅቱ ከመውሰድ ጀምሮ የፓርቲዎችን የክርክር መድረክ በአግባቡ መከታተላቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህም ለሀገርና ለህዝብ የተሻለ ሀሳብ ያለውን ፓርቲ ለመለየት እንዳስቻላቸው ገልጸው፤ ሀገርና ህዝብን በሰላምና ልማት ለሚያሻግር ፓርቲ ድምጼን ለመስጠት ተዘጋጅቼያለሁ ብለዋል።