የአፍሪካ ዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችውን አዲስ አበባን የሚመጥን የፖሊስ ሠራዊት ለመገንባት ውጤታማ ስራ እየተሰራ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችውን አዲስ አበባን የሚመጥን የፖሊስ ሠራዊት ለመገንባት ውጤታማ ስራ እየተሰራ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 19/2018 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችውን አዲስ አበባን የሚመጥን የፖሊስ ሠራዊት ለመገንባት ውጤታማ ስራ እየተሰራ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመልዕክታቸው፤ በየደረጃው የሚገኙ የአዲስ አበባ ከተማ የፖሊስ አመራሮች እና አባላት ባለፉት 100 ቀናት በዕቅድ የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎችን ማጠቃለያ ግምገማ ዛሬ ማካሄዳቸውን ጠቁመዋል።
በዚህ የግምገማ መድረክ ላይ የተገኙት ከንቲባዋ፤ ሠራዊቱ እያከናወናቸው ለሚገኙ ውጤታማ ተግባራት አድናቆታቸውን በመግለጽ አበረታተዋል።
ባለፉት 100 ቀናት በመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ በተያዙ የሪፎርም ዕቅዶች ላይ ያተኮሩ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውንም ገልጸዋል።
ይህም እየተከናወነ ያለው የሪፎርም ሥራ፣ እያደገችና እየዘመነች ከመጣችው የአፍሪካ እና ሶስተኛዋ የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችውን አዲስ አበባ የሚመጥን የፖሊስ ሠራዊት መገንባትን ያለመ መሆኑን ነው ያመለከቱት።
ተቋሙ ገለልተኛ ሆኖ በሕግና በሕዝብ የተጣለበትን አደራ በአግባቡ የሚወጣ፣ በሥነ-ምግባር ክብሩ የተጠበቀ፣ በሰው ኃይል አቋሙ ብቁ እንዲሁም በአሠራሩ ከዘመኑ ጋር የሚራመድ እንዲሆን ለማስቻል በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩና ሕዝቡ፣ አንዳንዶች የሚፈጽሙትን የተቋሙንና የሠራዊቱን ስም የሚያጠለሹ ስህተቶች እያረሙ፣ በጥሩ ሁኔታ የሚሠሩትን ደግሞ እያበረታቱ፣ ለሚከናወኑ መልካም ሥራዎች ሁሉ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።