በአዳማ ከተማ በተለያዩ ዘርፎች የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ነዋሪዎች ውጤታማ በመሆናቸው ለሌሎች ወጣቶችም የሥራ ዕድል ፈጥረዋል - ኢዜአ አማርኛ
በአዳማ ከተማ በተለያዩ ዘርፎች የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ነዋሪዎች ውጤታማ በመሆናቸው ለሌሎች ወጣቶችም የሥራ ዕድል ፈጥረዋል
አዳማ፤ ግንቦት 19/2018(ኢዜአ)፦ በአዳማ ከተማ በተለያዩ ዘርፎች የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ነዋሪዎች ውጤታማ በመሆናቸው ለሌሎች ወጣቶችም የሥራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውን ገለጹ።
ከተጠቃሚዎቹ መካከል አቶ ጌቱ ተስፋዬ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ከተማ አስተዳደሩ በቤተሰብ ብልጽግና ተደራጅተው ራሳቸውንና ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳደረገላቸው ገልጸዋል።
በከተማዋ ቦሌ ክፍለ ከተማ በተመቻቸላቸው የመሥሪያ ቦታ ላይ ከአምስት የቤተሰብ አባላት ጋር በመደራጀት በዚህ ዓመት ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
መንግሥት ባመቻቸላቸው የ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ብድር በዳቦ ማምረቻ ኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው ምርታቸውን ለአካባቢው ማኅበረሰብ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን አስረድተዋል።
አሁን ላይ ከራሳቸው አልፈው ለ10 ተጨማሪ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን አውስተዋል።
ሌላኛው በዱቄት ማምረቻ ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ገዙ በዳዳ በበኩላቸው፤ መንግሥት ወደ ልማት እንዲገቡ እንዲሁም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትልቅ እገዛ ማድረጉን ገልጸዋል።
ከተማ አስተዳደሩ የመሥሪያ ቦታ ከመስጠትና መሠረተ ልማት ከማሟላት ባለፈ፣ ከባንክ የ2 ሚሊዮን ብር ብድር እና የካፒታል ማሽን አቅርቦት እንዲያገኙ በማመቻቸት በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል።
አቶ ገዙና የቤተሰባቸው አባላት የዱቄት ማምረቻ ማኅበር በቀን 330 ኩንታል የስንዴ ዱቄት በማምረት ለዳቦ ፋብሪካዎችና ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ ይገኛሉ ብለዋል።
በዚህም ውጤታማ መሆን ከመቻላቸው ባለፈ ለስምንት ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ገልጸዋል።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የቤተሰብ ብልጽግና ፓኬጅ በከተማዋ በተደራጀ መልኩ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ይህ አሠራር እያንዳንዱን ቤተሰብ ለለውጥና ለዕድገት በማነቃቃት፣ ለመበልፀግ በቁጭት እንዲነሱ ማድረጉን ጠቁመው፤ ተሳታፊዎች የጠራ ግንዛቤ ይዘው ሥራ ውስጥ እንዲገቡ እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
በበጀት ዓመቱ ለቤተሰብ ብልጽግና ተሳታፊዎች የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባው፤ ለዚህም አስተዳደሩ የመሥሪያና የመሸጫ ቦታዎችን እንዲሁም የብድር አቅርቦትን ለማመቻቸት እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በዚህ ዓመት በከተማዋ በተገነቡ በርካታ ሼዶች 89ሺህ የከተማዋ ወጣቶችና ነዋሪዎች በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ዘርፎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆን ችለዋል ብለዋል።