ሀዋሳ ከተማን ለነዋሪዎች ምቹ እና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ የሚያደርጉ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ሀዋሳ ከተማን ለነዋሪዎች ምቹ እና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ የሚያደርጉ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጠናክሮ ይቀጥላል
ሀዋሳ፤ ግንቦት 19/2018(ኢዜአ)፦ ሀዋሳ ከተማን ለነዋሪዎች ምቹ እና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ የሚያደርጉ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ከከተማው ከንቲባና ከተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ጋር በመሆን፤ በከተማዋ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በምረቃው መርሃ ገብር እንዳሉት፤ የለውጡ መንግስት ለከተሞች በሰጠው ልዩ ትኩረት የከተሞችን ዕድገት የሚያፋጥኑ ዘርፈ-ብዙ የልማት ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በዚህም ሀዋሳን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ለቱሪዝምና ለኢንቨስትመንት ደግሞ ተመራጭ ለማድረግ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በከተማዋ የተመረቁት የልማት ፕሮጀክቶች በኮሪደር ልማት የተጀመሩ ሥራዎችን ከማጠናከር ባለፈ፤ የአገልግሎት አሰጣጥን በማሳለጥ የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የሚመልሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የክልሉ መንግስት ሀዋሳን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ለቱሪዝም መስህብ ልማቶችና ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ማስፋፊያ ልዩ ትኩረት መስጠቱንም አንስተዋል።
የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው፤ የሀዋሳን የኮሪደር ልማትና ሁሉን አቀፍ የልማት ፕሮጀክቶች በማፋጠን ከተማዋን የቱሪዝምና የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማዋ በመደመር እሳቤ የሚከናወኑት የልማት ፕሮጀክቶች በተለይም በጥራት ላይ ማተኮራቸውን አብራርተዋል።
ዛሬ ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ የአዳሬ አጠቃላይ ሆስፒታል ማስፋፊያ፣ የአጠቃላይ ትምህርት ቤቶች ማስፋፊያ ግንባታ እና ሌሎች መሰረተ-ልማቶች ይገኙበታል ብለዋል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው መሆኑን ከንቲባው አስታውቀዋል።
የሃዋሳ ከተማ ነዋሪዋ ሲስተር እልፍነሽ ናኡሼ፤ በሃዋሳ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች ከተማዋን አዲስ ገጽታ እያላበሷት መሆኑንና የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለነዋሪዎች አዲስ የሥራ ዕድል እየፈጠሩ እንደሚገኙ አክለዋል።
ሌላኛው የከተማው ነዋሪ አቶ ተስፋዬ አበባው፤ ዛሬ በከተማዋ የተመረቁት ፕሮጀክቶች በተለይም በጤናው ዘርፍ የነበሩትን ውስንነቶች ከመቅረፍ አንጻር ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።
በምረቃ መርሃ-ግብሩ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፣ የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና የሕብረተሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።