የአካል ጉዳተኞች ማኅበራዊ አካታችነት ለሁለንተናዊ እድገት - ኢዜአ አማርኛ
የአካል ጉዳተኞች ማኅበራዊ አካታችነት ለሁለንተናዊ እድገት
በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞችን ማኅበራዊ አካታችነት ማረጋገጥ ለሀገር ግንባታ፣ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፈንና ለዘላቂ ሰላም መሠረት መሆኑ ይታመናል። በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ከ20 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች እንደሚኖሩ የሚገመት ሲሆን፣ ይህን ያህል የኅብረተሰብ ክፍል ያገለለ የልማት ጉዞ ሰብአዊ ዕሴቱ የጎደለና ፍትሐዊነት የራቀው ነው። በመሆኑም መንግሥት አካል ጉዳተኝነትን ዝቅ አድርጎ የመመልከት የተሳሳተ አመለካከትን በመቀየር፣ እነዚህ ዜጎች በሁሉም የሥራ ዘርፎች የላቀ ውጤት ማሳየት የሚችሉ የሀገር ባለቤትና ገንቢዎች መሆናቸውን በመገንዘብ የአካታችነት መርህን እየተገበረ ይገኛል። ማንኛውንም በአካል ጉዳተኝነት ላይ የተመሠረተ አድልዎ መከላከልና እኩል የሕግ ጥበቃ እንዲያገኙ ማድረግ የመንግሥት ዋነኛ አቋም ነው።
ባለፉት ዓመታት የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ስፋት ያላቸው ተግባራት ተከናውነዋል። በተለይም ዜጎች በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ሥራ ትኩረት ተሰጥቶታል። የአካል ጉዳተኞችን የእንቅስቃሴ ችግር ለመቅረፍ እንዲቻል የሰው ሠራሽ አካልና የአካል ድጋፍ ማምረቻ ማዕከላትን የማዘመን ሥራ ተሠርቷል። ለዚህም በዘርፉ የተሃድሶ የልህቀት ማዕከል ተገንብቶ አገልግሎት እንዲጀምር የተደረገ ሲሆን፣ ከ5 ሺህ በላይ አካል ጉዳተኞች ከቀረጥና ታክስ ነፃ የሆኑ ተሸከርካሪዎችን ከውጭ በማስገባት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል። ይህ አገልግሎት በማዕከል ብቻ ሳይወሰን በክልሎች ጭምር ተደራሽ እንዲሆን በማድረግ በክልሎች ለሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የአካላዊ ተሃድሶ ድጋፍ ተሰጥቷል።
የአገልግሎት አሰጣጡን ይበልጥ ቀልጣፋ ለማድረግም ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የዲጂታል (ኢ-ሰርቪስ) አሠራር ተግባራዊ ሆኗል። ይህም አካል ጉዳተኞች የሚፈልጉትን መረጃና አገልግሎት በፍጥነት እንዲያገኙ አስችሏል። ከዚህ በተጨማሪ አካል ጉዳተኞች በማኅበር ተደራጅተው መብቶቻቸውን እንዲያስከብሩና በፈጠራ ሥራዎች እንዲሰማሩ የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፎች ሲደረጉ ቆይተዋል። መንግሥት የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል በሚያደርገው ጥረት የአካል ጉዳተኞችንና አቅመ ደካማ ወገኖችን ቤት በማደስ እንዲሁም በከተሞች የምገባ ማዕከላትን በማስፋፋት "ማንንም ወደኋላ እንዳይቀር" የሚለውን መርሕ በተግባር ሲያሳይ ቆይቷል።
መንግሥት የአካል ጉዳተኞችን መብት ይበልጥ የሚያስከብሩ የሕግና የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግ ለመስራት አቅዷል ። አካል ጉዳተኞች ከድህነት እንዲወጡና የትምህርት ሽፋናቸው እንዲያድግ ልዩ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ። በተለይም በሥራ ስምሪት ረገድ ያላቸውን መብት በማረጋገጥ፣ በፖሊሲ ቀረጻና በስትራቴጂ አተገባበር ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል ።
የማኅበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ስለ አካል ጉዳተኝነት የሚታየው አዎንታዊ አመለካከት እንዲጠናከርና ፍትሕ የሰፈነበት አካታች ማኅበረሰብ እንዲገነባ በትጋት ይሠራል። መንግሥት የጀመራቸውን ግዙፍና አካታች ፕሮጀክቶች በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ፣ የአካል ጉዳተኞችን ደህንነት፣ ጤንነትና ውጤታማነት የሚያረጋግጥ የብልፅግና ጉዞን በጋራ ማሳካት አስፈላጊ ነው።