ቀጥታ፡

የአረፋ በዓል የመተሳሰብ፣ የፍቅርና የአንድነት መገለጫ ነው

ወላይታ ሶዶ/ዲላ፤ ግንቦት 19/2018(ኢዜአ)፦ የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል የመተሳሰብ፣ የፍቅርና የአንድነት መገለጫ መሆኑ ተመለከተ።

1ሺህ 447ኛ የኢል አል አድሃ (አረፋ) በዓል በወላይታ ሶዶ እና በዲላ ከተሞች በሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ተከብሯል።


 

በወላይታ ሶዶ ከተማ የሐምዛ መስጂድ ዋና ኢማም ኡስታዝ ሼህ አሊ ሀምዛ ለኢዜአ እንደገለጹት የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል የመተሳሰብ፣ የፍቅርና የአንድነት መገለጫ ነው።

ምዕመናን ፍቅርና አንድነትን በማጠናከር ኃይማኖታዊ ትዕዛዙን በመፈጸም የሚያከብሩት መሆኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም በቤተሰባዊነት፣ በይቅርታና ሰላምን በሚያጠናክሩ ተግባራት የሚከበር መሆኑን ጠቁመው ሙስሊሙ ህብረተሰብም ይህንኑ ሊፈጽም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።


 

የወላይታ ዞን ከፍተኛ ሸሪአ ፍርድ ቤት ቃዲ ሼህ ጁዋር ሀሚድ በበኩላቸው ኢድ አል አድሃ በዓል በሀይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ አንድነትን ይበልጥ በማጠናከር የተቸገሩትን በመርዳትና ከጎረቤቶች ጋር በደስታ የሚከበር መሆኑን ተናግረዋል።


 

በዓሉ መልካም ተግባራትን በማከናወንና እርስ በርስ በመደጋገፍ እንዲሁም ያለውን በመካፈል የሚከበር መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ አቶ አኑዋር አበራ እና ጃፍር አብድሽኩር ናቸው።


 

በተያያዘም በዲላ ከተማ የቢላል መስጅድ ኢማም ኡስታዝ ሸህ ሱፍያን ጀማል አረፋ የመረዳዳት እሴት የሚጎላበት በዓል መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

የኢድ አል አደሃ (አረፋ) በአል ያለንን ተካፍለን ማሳለፍን የምንማርበት ነው ያሉት ደግሞ  የዲላ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ሰብሳቢ ኡስታዝ አብዱረህማን አብዱቄ ናቸው።


 

በአሉ ሲከበር ይህንን መንፈሳዊ እሴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም