ቀጥታ፡

የነገሌ ቦረና ገዳ አውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎት መጀመር የአካባቢውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የበለጠ ያነቃቃል

ነገሌ ቦረና፤ ግንቦት 19/2018(ኢዜአ)፦ የነገሌ ቦረና ገዳ አውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎት መጀመር የአካባቢውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የበለጠ የሚያነቃቃ መሆኑን የዞኑ ነዋሪዎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ አየር መንገድ 24ኛ የሀገር ውስጥ መዳረሻ የሆነውንና አዲሱን የነገሌ ቦረና ገዳ አውሮፕላን ማረፊያን ዛሬ በይፋ መርቀዋል።




ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው እንደ ቦይንግ 737 ማክስ ያሉ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን የማስተናገድ አቅም ያለው ይህ ዘመናዊ አውሮፕላን ማረፊያ፤ የአካባቢውን እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ የንግድ ልውውጥን እና ቱሪዝምን የማሳደግ ራዕይን ሰንቆ በሳምንት ሦስት በረራዎችን የሚያስተናግድ ነው ብለዋል።

በምስራቅ ቦረና ዞን የተገነባው ይኸው የነገሌ ቦረና ገዳ አውሮፕላን ማረፊያ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ፣ ምቹ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት እንደሚያስችላቸው የዞኑ ነዋሪዎች ገልጸዋል።




የነገሌ ቦረና ከተማ ነዋሪው እንዳለ መገርሳ እንደገለጹት፤ የአውሮፕላን ማረፊያው በየብስ ትራንስፖርት ረጅም ጉዞ ምክንያት ይደርስ የነበረውን እንግልትና ችግር በእጅጉ ያቃልላል።

ዞኑ በእንስሳት ሀብትና የስንዴ ምርት የሚታወቅ ቢሆንም፣ ምርቱን ለማጓጓዝ የትራንስፖርት እጥረት ያጋጥም እንደነበር አስታውሰው፣ አውሮፕላን ማረፊያው የምርት ዝውውርን የበለጠ ያቀላጥፋል ብለዋል።

ይህም ለአካባቢው ኢኮኖሚና ቱሪዝም እድገት ካለው አስተዋጽኦ ባሻገር የመንገደኞችን ጉዞ ምቹ፣ ቀላልና ፈጣን እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

በዘመናዊ ትራንስፖርት ለመጠቀም የነበራቸው ምኞት በመሳካቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል።




ሌላው የነገሌ ቦረና ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ ፈንታ ገረመው በበኩላቸው፤ የአውሮፕላን ማረፊያው ስራ መጀመር የዞኑን ልማትና እድገት እንደሚያፋጥን ገልጸዋል።

በተለይም የነገሌ ቦረና ከተማን የንግድና የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አብራርተዋል።




ሌላው በዞኑ ሊበን ወረዳ ነዋሪ ቢሉ ቢርቢርሳ የአውሮፕላን ማረፊያው መንግስት ለአርብቶ አደሩ አካባቢ የሰጠውን ትኩረትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን አንስተዋል።

ለአካባቢው ወጣቶች ሰፊ የስራ እድል እንደሚፈጥር፣ የግብርና ምርቶችና ግብአቶች በወቅቱና በፈጣን ሁኔታ እንዲጓጓዙ እንደሚረዳና ባለሀብቶች እንዲሁም ተጓዦች ወደ ዞኑ በቀላሉ እንዲመጡ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ጠቅሰዋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ የፌደራል፣ የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ በርካታ ቁጥር ያለው የዞኑ ህዝብ ተገኝቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም