ቀጥታ፡

በአረፋ በዓል ጎልቶ የሚታየውን የአብሮነትና የመደጋገፍ እሴት አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል

ወልቂጤ/ሆሳዕና፤ ግንቦት 19/2018(ኢዜአ)፦ በአረፋ በዓል ጎልቶ የሚታየውን የአብሮነትና የመደጋገፍ እሴት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ገለጸ።

1ሺህ 447ኛው የኢድ አል አድሀ (አረፋ) በዓል በወልቂጤ እና በሆሳዕና ከተሞች በድምቀት ተከብሯል።

በከተሞቹ ያሉ የሃይማኖቱ ተከታዮች የመታዘዝና የመተዛዘን ተምሳሌት የሆነውን የአረፋ በዓል የሌላቸውን ወገኖች በማገዝ በደስታ እያከበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ኡስታዝ በህጃ አብዱልጀሊል በእዚህ ወቅት እንዳሉት፣ የአረፋ በዓል የአብሮነት እሴቶች የሚጎሉበት በመሆኑ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ቦታ አለው።

የሌላቸውን ወገኖች በማሰብ በዓሉን በጋራ በደስታ ማክበር ከእምነቱ ተከታዮች እንደሚጠበቅ ገልጸው፤ በዓሉ ያለውን የሰላም፣ የፍቅርና የመተሳሰብ እሴት በማጎልበትና መልካም ተግባር በመፈጸም ማሳለፍ እደሚገባ አስገንዝበዋል።


 

የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል የእርስ በእርስ መደጋገፍ የሚጎላበትና ሰላም የሚሰበክበት ታላቅ በዓል ነው ያሉት ደግሞ የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ ሙራድ ያሲን ናቸው።

የበዓሉ የአብሮነት እሴቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የከተማው አስተዳደር የበኩሉን እየተወጣ መሆኑንም ተናግረዋል።


 

ከበዓሉ ተዳሚዎች መካከል ሲራጅ ኑራን እንዳሉት፣ አረፋ እርድ የሚከወንበት በዓል በመሆኑ ያለው ከሌለው ጋር ተካፍሎ የሚበላበት፣ መተዛዘንና አብሮነት ጎልቶ የሚታይበት ነው።


 

በዓሉን ስናከብር ፈጣሪ የሚወደውን በጎ ተግባር በመፈጸም፣ የተቸገሩና አቅመ ደካሞችን በማሰብ መሆን እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ አብዱራህማን ጀማል የተባሉ ታዳሚ ናቸው።

በተመሳሳይ የአረፋ በዓል በሆሳዕና ከተማ አብዮ ኤርሳሞ መታሰቢያ ስታዲየም በተለያዩ ሀይማኖታዊ ሥርዓቶች ተከብሯል።


 

በበዓሉ ላይ የሀድያ ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ኡስታዝ ሱልጣን ኡስማን እንደገለጹት፣ የአረፋ በዓል የመስዋዕትነት፣ የእዝነትና የርህራሄ በዓል ነው።

በመሆኑም ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን በአቅራቢያው ያሉ አቅመ ደካሞችን በመርዳትና አብሮነቱን በሚያጠናክር መልኩ ማክበር እንዳለበት አስገንዝበዋል።


 

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ወጣት ነጃት አበበ በሰጠችው አስተያየት የመታዘዝና የመተዛዘን ተምሳሌት የሆነውን የኢድ አል አደሃ በዓልን የሌላቸውን ወገኖች በመጠየቅና በማገዝ በደስታ እያሳለፈች መሆኗን ተናግራለች።

የሀይማኖቱ አስተምህሮ በሚያዘው መሰረት አቅመ ደካማ ወገኖችን በመደገፍ እያሳለፉ መሆናቸውን የተናገሩት ሌላኛው የከተማ ነዋሪ ደግሞ አቶ አብድልፈታ ቢላል ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም